በትራምፕ ዳኛ ላይ የግድያ ዛቻ የሰነዘረችው አሜሪካዊት በቁጥጥር ሥር ዋለች

ዛቻ የደረሰባቸው ጥቁሯ ዳኛ

የፎቶው ባለመብት, United States Courts Service

የምስሉ መግለጫ, ዛቻ የደረሰባቸው ጥቁሯ ዳኛ ታንያ ቹትካ

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የወንጀል ክሶችን የፍርድ ሂደት እየዳኙ የሚገኙትን ጥቁር ሴት ዳኛ እገድላለሁ ብላ የዛተችው ሴት ክስ ተመሰረተባት።

የቴክሳስ ተወላጅ የሆነችው አቢጌል ጆ ሽሪ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ፍርድ ቤት ደውላ ዳኛዋን ታንያ ቹትካን “ዘረኝነት የተሞላበት አጸያፊ ስድቦች” ሰድባለች እንዲሁም አስፈራርታለች ተብሏል።

በተጨማሪም የዲሞክራት ፓርቲ ተወካይ በሆኑ የምክር ቤት አባል ላይም እንዲሁም የግድያ ዛቻ ማድረሷም ተገልጿል።

የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚያመለክተው መርማሪዎች ስልክ ቁጥሯን ተከታትለው ከደረሱበት በኋላ ግለሰቧ ለፍርድ ቤቱ ስልክ መደወሏን አምናለች።

ግለሰቧ ለፍርድ ቤቱም ስልክ ደውላ የትራምፕን የምርጫ የማጭበርበር ክስ የሚከታተሉትን ይህችን ጥቁር ሴት ዳኛ “በእኛ ዕይታ ክትትል ውስጥ ነሽ። ልንገድልሽ እንፈልጋለን” በማለት አስፈራርታለች ተብሏል።

አቃብያነ ሕግ እንዳለውም “ትራምፕ በመጪው 2024 ካልተመረጠ እንገልሻለን” ማለቷም ተገልጿል።

ከዳኛዋ በተጨማሪም በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ያሉ ሁሉንም የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ደዋይዋ ማስፈራራቷን የፍርድ ቤት መዝገብ ያስረዳል።

በተጨማሪው ለሂውስተን ከተማ በከንቲባነት የሚወዳደሩት ጥቁር የዲሞክራት ፓርቲ ተወካይ እና የምክር ቤት አባል በሆኑት ሸይላ ጃክሰንም ሊ ላይ የመግደል ዛቻ አድርሳለች ተብሏል።

ከሦስት ቀናት በኋላ የፌደራሉ መርማሪዎች ግለሰቧ ወደምትኖርበት ሂውስተን ግዛት አልቪን የተሰኘ አካባቢ ሲሄዱም ዛቻዎቿን ለመፈጸም ወደ ዋሽንግተን የመሄድ ፍላጎት እንዳልነበራት መናገሯን የፍርድ ቤቱ ክስ ያስረዳል።

ሆኖም “ ሸይላ ጃክሰን ሊ ወደ አልቪን ከመጣች ሁኔታዎች ቀለሉ” ማለቷም ሰፍሯል።

ግለሰቧ የማስፈራሪያ ጥሪውን ከማድረጓ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “በእኔ ላይ ከመጣችሁ ፤ እኔም አልለቃችሁም” የሚል የማስፈራሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ትራምፕ በምርጫ ማጭበርበር በርካታ ክሶች እየቀረቡባቸው ይገኛሉ።

ባለፈው አርብ ዳኛ ታንያ በፍርድ ቤት ችሎት ላይ ሁለቱም ወገኖች ነገሮችን ከሚያባብሱ እና ከሚያቀጣጥሉ ጉዳዮች እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።