20 ዶላር ለማዳን ወንዝ የገባው ላይቤሪያዊ ሰምጦ ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
20 ዶላር ለማውጣት ወንዝ የገባው ወጣት ሕይወት ተቀጠፈ
አሳዛኝ አጋጣሚ ነው፡፡
ይህ ወጣት በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ ነዋሪ ነው፡፡ ክፉ አጋጣሚ፤ ድልድይ ሲሻገር 20 ዶላር ወደቀበት፡፡
20 ዶላሯ በንፋስ ተንከላውሳ ወንዝ ውስጥ ስትገባ ተመለከታት፡፡ አላስቻለውም፡፡ ዘሎ ገባ፤ ተከተላት፡፡
ስሙ ታምባ ላሚኔ ይባላል፡፡ ቸርቻሪ ነው፤ የጎዳና ለፍቶ አዳሪ፡፡
የሚደንቀው ታዲያ ሰምጦ አልቀረም፡፡ 20 ዶላሯን ይዟት ወጣ፡፡ ተሰብስበው ሁኔታውን ይመለከቱ ለነበሩ ሰዎችም አሳያቸው፡፡
ከዚያ ግን ድንገት ተመልሶ ሰመጠ፡፡
ላሚኔ 20 ዶላሯትን ተከትሏት ወንዝ ሲገባ ከጓደኛው ጋር በእግር እየተጓዙ ነበር፡፡ ድልድዩ ላይ ሲደርሱ ግን እንዴት ዶላሯ ከእጁ እንዳመለጠች አልታወቀም፡፡
ገንዘቡን ማዳን የፈለገው አብሮት ለሚሰራው ጓደኛው ለመክፈል ነው፡፡ እዳ ነበረበት፡፡ ከ20 ዶላሩ 5ቱ ዶላር የሱ አይደለም፡፡ ለመስጠት ብሎ ነው፡፡
5ቱን ዶላር የሚመልሰው ሁለቱ ጓደኛሞች አንድ በጋራ የሰሩት ‹ሽቀላ› ነበር፡፡ ትርፉን ሊጋሩ ተስማምተው ነበር፡፡
ላሚኔ በዚህ መንገድ ሕይወቱን ማጣቱ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡
ላይቤሪያ ከአሜሪካና ከካሪቢያን በግፈኛና ዘረኛ ነጮች ነጻ የተደረጉ የቀድሞ ‹ባሪያዎች› የተፈጠረች አገር ናት፡፡
በዚያች አገር የአሜሪካን ዶላር ከላይቤሪያ ገንዘብ ጋር ጎን ለጎን አገልግሎት ይሰጣል፡፡
አሁን አሁን የዶላር ዋጋ ለላይቤሪያ ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር በከባድ ሁኔታ እየጠነከረ በመምጣቱ ዶላር ትልቅ ዋጋ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡
የላሚኔ ሬሳ እንስከሁን አልተገኘም፡፡
ሰምጦ የቀረው በመሱራዱ ወንዝ ውስጥ ነው፡፡ ወንዙ ከሞንሮቪያ ተነስቶ በሽሮድ ደሴት ይዘልቃል፡፡
የዶላሩንና የወጣቱን ሁኔታ ለማየት የተሰበሰበው ሰው ላሚኔ 20 ዶላሯን ከፍ አድርጎ ለአፍታ ሲያሳያቸው ገንዘቡም እሱም ተርፈዋል ብለው ተደስተው ነበር፡፡ያጨበጨቡም ነበሩ፡፡
ነገር ግን ከአፍታ ቆይታ በኋላ ላሚኔ በዚያው ሰምጦ ቀርቷል፡፡ 20 ዶላሩን እንደዚያው፡፡
የላሚኔ ሞት በሞንሮቪያ ከፍተኛ ሐዘን መፍጠሩን የቢቢሲ ዘጋቢ ጽፏል፡፡












