በፈረንሳይ በዩቲዩብ ሚሊዮነር የሆኑ ሕጻናትን የሚመለከት ሕግ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ ትንንሽ ልጆች ሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆናቸው የተነሳ ሚሊዮነር የሆኑ ልጆችን ደህንነት የሚጠብቅ ሕግ አውጥታለች፡፡
እነዚህ ትንንሽ የማኅበራዊ ሚዲያ ዝነኞች ዕድሜያቸው ክፉና ደጉን ስለማይለይ ለጉዳት እንዳይጋለጡ በሚል ነው ሕጉ የወጣው፡፡
ለምሳሌ እነዚህ ልጆች እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያገኙ ገንዘቡ የማን ነው? እንዴትስ መተዳደር ይገባዋል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ሕጉ ዝርዝር መመርያን ይዟል፡፡
ልጆቹ ዝነኛ ከሆኑ በኋላ ዝናቸው እንዲያበቃና እንደማንኛውም ልጅ መሆን ቢፈልጉስ የሚለውም በአዲሱ ሕግ ተካቷል፡፡
የመረሳት መብታቸውን የሚያስጠብቀው ይህ ሕግ ዝነኛ ልጆች አንድ ጊዜ ታዋቂ ከሆኑ በኋላ እውቅና በቃን ቢሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ምሥላቸውን ማውረድ፣ መዝጋት፣ አልያም መሰረዝን ይገደዳሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትንንሽ ልጆች ከመጠን በላይ ዝነኛ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ይህን ዝናቸውን ተከትሎም ትልልቅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ማስታወቂያ ያሠሯቸዋል፡፡
በተለይ በዩትዩብ ሚሊዮኖች በቀን በቀን የሚከታተሏቸው አዳጊ ዝነኞች በርክተዋል፡፡
ፈረንሳይ በዚህ ረገድ እነሱን ለመከላከል ያወጣቸው ሕግ አድናቆትን አግኝቷል፡፡ ፈር ቀዳጅም ተብሏል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና ከዚህ ሕግ መጽደቅ ጀርባ ሲሠሩ የነበሩት ብሩኖ ስቱደር ለሉ ሙንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት ሕጉ ለሌሎች አገሮችም እንደመነሻ ሊጠቅማቸው ይችላል፡፡
ትናንትና በሙሉ ድምጽ ነው የጸደቀው ይህ ሕግ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ ሁሉንም ልጆችን የሚመለከት አይደለም፡፡ ረዥም ሰዓት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያጠፉና ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈላቸው ትንንሽና አዳጊ ዝነኞችን ብቻ የሚመለከት እንጂ፡፡
ሕጉ በሞዴልነትና በተዋናይነት የሚሠሩ ሕጻናት የሚያገኙትን ዓይነት መብት በማኅበራዊ መዲያ ዝነኛ ለሆኑ ሕጻናትም የሚሰጥ ነው፡፡
ልጆቹ የዚህ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት 16 ዓመት እስኪሞላቸው ብቻ ነው፡፡
አንድ ኩባንያ ልጆቹን ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሎ ማስታወቂያ ለማሠራት መጀመርያ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፍቃድ ማግኘት አለበት፡፡
የምክር ቤት አባሉ ሚስተር ስቱደር፣ የልጆች መብት መጠበቅ ያለበት ከበይነ መረብ ውጭ ብቻ አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ሕግ አልባ ዓለም መሆን አይኖርበትም ብለዋል፡፡
ፎርብስ መጽሔት በዩትዩብ ሚሊዮነር የሆኑ ሕጻናትን ዝርዝር ማውጣት ጀምሯል፡፡
አሜሪካዊው የ8 ዓመት ልጅ ራየን ካጂ በዩትዩብ አሻንጉሊቶችን በተመለከተ ለሚያቀርበው ሒስ 26 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት የዓለም የልጅ ሀብታም ሆኗል፡፡
ናስቲያ በሚል የቁልምጫ ስም የምትታወቀው የሩሲያ ተወላጇ ሕጻን አናስታሲያ ራዲዝንካያ ወደ 18 ሚሊዮን ዶላር በማጋበስ ሌላኛዋ ሥመጥር ናት፡፡
ናስቲያ ገና 6 ዓመቷ ነው፡፡












