በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ምዝገባ በቅርብ ጊዜ እንደሚጀመር ተገለፀ

ከጥቂት ወራት በፊት በፓርላማ የፀደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንዳሉ የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአፍሪካ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ያላቸው ሰዎች የሚያሳውቁበት ወይንም ለሕጋዊ አካላት የሚያስረክቡበት ወርን በማስመልከት የሰላም ሚኒስቴር ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና አስተዳደርን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ በሰጡበትም ወቅት ነው ይህ የተገለፀው።
በአፍሪካ ውስጥ የሕገወጥ መሳሪያዎች ከቀላል ወንጀሎች እስከ ሽብር ተግባር የሚፈፀምባቸው እንደሆነ የሰላም ሚኒስቴሯ ሙፈርያት ካሚል ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም ሕገወጥ የጦር መሳሪያ በመቆጣጠር እንዲሁም ሰላም ለማስፈን ኅብረተሰቡን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በማሳተፍ እየተሰራ እንደነበር ጠቁመዋል።
"እስካሁን ባለው አሰራር የሕገወጥ መሳሪያ ዝውውርን መቆጣጣር ያለባቸው ተቋማት የሚፈለገው የቴክኖሎጂ እገዛ የላቸውም" ያሉት ሚኒስትሯ፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በፌደራል ደረጃ ያሉ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በቅርብም ምዝገባ የሚጀመር መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስልጠናውን በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች ላሉ ባለሙያዎች በመስጠት አዋጁን በአገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ ለማዋል እንደሚሰራም ተገልጿል።
አዋጁ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ተከብሮ ሰላማዊ እና መረጋጋት የሰፈነበትን ኅብረተሰብ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ሚኒስትሯ ጨምረው ተናግረዋል።
የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚቀጥል ከሆነ "ሰላም ጠፍቶ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር" የተናገሩት ሚኒስትሯ ኅብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን እንዲቆምም በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ምን እየተሰራ ነው?
የሰላም ሚኒስቴር አማካሪ አሆኑት አቶ ሚናስ ፍሰሃ ኢትዮጵያ እኤአ በ2004 የአነስተኛ ጦር መሳሪያዎች መከላከልና ቁጥጥር (ናይሮቢ ፕሮቶኮል) መፈረሟን አስታውሰው፣ ለረዥም ዓመታት ሕግ ሳይኖራት እንደቆየች ተናግረዋል።
ይሁንና መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት በታሕሳስ 2012 የጦር መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012 እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህንንም አዋጅ ወደ ተግባር ለመቀየር ደንቦችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው መጠናቀቁን አማካሪው ጨምረው ገልፀዋል።
"የሕዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እንደሆነ ይታመናል" ያሉት አቶ ሚናስ ይሁንና ዜጎች ባላቸው የማኀበራዊና ባህላዊ እሴቶች፣ ለደህንነታቸው እንዲሁም በስራቸው ምክንያት ጦር መሳሪያ እንዲይዙ ግዴታ ሲሆንባቸው በሕጉ ላይ በተቀመጠው መሰረት የጦር መሳሪያ እንዲይዙ ይፈቀድላቸዋል ሲሉም በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና ምዝገባ ስራውን በበላይነት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሰራ መታቀዱት የተናገሩት አቶ ሚናስ፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳር ፖሊስ ኮሚሽኖች በፌደራል ፖሊስ በሚሰጣቸው ውክልና መሰረት እንደሚሰሩ ተነግሯል።
ይሁን እንጂ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የሕገወጥ መሳሪያ ሁኔታ እንዲሁም ምዝገባው መቼ እንደሚጀመር የተባለ ነገር የለም።
ጦር መሳሪያን መታጠቅ የሚችለው ማን ነው?
አዋጁ ማን የጦር መሳሪያ መታጠቅ እንደሚችል እና እንደማይችል በግልፅ እንዳስቀመጠ የሚናገሩት አቶ ሚናስ ፍሰሃ ሙሉ ለሙሉ ወይንም በከፊል የሕግ ብቃት የሌላቸው ሰዎች፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይንም ባለባቸው የአካል ጉድለት ምክንያት የተከለከሉ የጦር መሳሪያ መጠቀም እንደማይችሉ ሕጉ ላይ ሰፍሯል ብለዋል።
ሌላኛው አዋጁ የጦር መሳሪያ ያላቸው አስመዝግበው ፈቃድ እንዲኖራቸውና እንዲጠቀሙ ከማስቻል ጎን ለጎን ከአንድ የጦር መሳሪያ በላይ ያላቸው ሰዎችም በአካባቢያቸው በሚገኘው የፖሊስ ጽህፈት ቤት አማካኝነት እንዲመልሱ የሚያደርግ መሆኑንም አቶ ሚናስ ይናገራሉ።
የጦር መሳሪያ ምዝገባው የሚካሄደው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚሆንም ተናግረዋል።












