በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምልክት ከታየባቸው አራቱ ነፃ ሆነው መገኘታቸው ተነገረ

ጤና ቢሮ

በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው ከነበሩ ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ ነፃ መሆናቸው የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የቫይረሱ ምልክት ታይቶባቸው ከነበሩት መካከል የሁለቱ ውጤት እንደታወቀ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ዛሬ በባሀርዳር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ለሶስተ መቶ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም አምስት የለይቶ ማቆያዎች ብቻ እንደነበሩ የገለጹት ኃፊው በሁሉም ዞኖች አንድ አንድ የለይቶ ማቆያ ቦታ እንዲዘጋጅ መደረጉንም ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ አራት አውሮፕላን ማረፊያዎች እና በመተማ ድንበር እስካሁን 1900 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሙቀት ምርመራ ማድረጉን ቢሮው አስታውቋል።

በክልሉ በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን እንደ መልካም ዕድል መጠቀም ዝግጅቶችን አጠናክሮ ማካሄድ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ ኃይሌ ናቸው።

ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካላት በመከታተል እና የግል ንጽህናውን አዘውትሮ በመጠበቅ የመከላከል ሥራውን ከእራስ መጀመር እንደሚገበባ አስረድተዋል።

ከአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር በተጨማሪ የክልሉ መግቢያ በሆኑት በደጀን፣ ደብረ ብርሃን እና ባቲ የሙቀት መለካት ሥራ ከሰኞ ጀምሮ ተግበራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የቫይረሱን ምርመራ በክልሉ ለመጀመር የሚመለከታቸውን አካላት እየጠየቁ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ የሚሆን ግብዓት ከተገኘ ዝግጁ የሆነ ቤተ-ሙከራ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ በክልሉ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳደድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ጠቁመው፤ ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

የክልሉን ከፍተኛ ሥራ ኃፊዎች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የሚመለከታቸው አካላት የተዋቀሩበት ግብረ-ኃይል ወደ ሥራ ገብቷል።

የክልሉ መንግሥትም ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ ሥራዎች የሚውል 150 ሚሊዮን ብር መመደቡን ታውቋል።