በጣሊያን በኮሮናቫይረስ በአንድ ቀን ብቻ 475 ሰዎች ሞቱ

ጣሊያን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ሙሉ በሙሉ አንቅስቃሴ ከከለከለች ሁለት ሳምንት እየሞላት ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጣሊያን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ሙሉ በሙሉ አንቅስቃሴ ከከለከለች ሁለት ሳምንት እየሞላት ነው

በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 475 ሰዎች በአንድ ቀን ብቻ መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ። ይህ ቁጥር ቫይረሱ ከተከሰተ ትልቁ ነው የተባለ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥርንም ወደ 3ሺህ አድርሶታል።

በጣሊያን በአሁኑ ሰአት 35,713 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከበሽታቸው ያገገሙት 4ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው።

ሎምባርዲ በምትሰኘውና ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ግዛት በአንድ ቀን የ319 ሰዎች ሞት መመዝገቡ ይታወሳል።

ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃች አገር ጣሊያን ናት። በዓለማችን ላይ ከ8ሺህ 758 ያህል ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኛው ቁጥር ያለው ሞት የተመዘገበው በቻይና ነው።

በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእስያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ቫይረሱ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ በርካታ የዓለማችን አገራት የተለያዩ እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ ይገኝበታል።

ይህ እርምጃም የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት ባሻገር በጤና ባለሙያዎች ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትናንት በሰጡት መግለጫ አገራት የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር " ምልክቱን የሚያሳዩ ሰዎችን መለየት፣ መመርመር፣ ማከምና ንክኪዎችን መለየት" ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ጣሊያን ቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ሙሉ በሙሉ አንቅስቃሴ እንዳይኖር ከከለከለች ሁለት ሳምንት እየሞላት ነው።

ከጣሊያን ውጪም በስፔን 13716 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 598 ደግሞ መሞታቸው ተመዝግቧል።

በማድሪድ በሚገኝ አንድ የአቅመ ደካሞች እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ 17 ነዋሪዎች መሞታቸውን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩም ተገልጿል።

በፈረንሳይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 7730 የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 175 መሆኑ ተነግሯል።

በዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ የተያዙ 104 ሰዎች ሞተዋል።

በአውሮፓ ሕብረት ከአባላት አገራት ዜጎች ውጪ ወደ አውሮፓ በአውሮፕላን፣ በየብስም ሆነ በባህር የሚመጡ በሙሉ ለ30 ቀን ያህል እንዳይገቡ ክልከላ ተቀምጧል።

ይህ እገዳ አውሮፓ ሕብረት አባል አገራትን እንእቅስቃሴ የማይጨምር መሆኑ ተገልጿል።

ኮሮና