ኬንያዊው ኮሮናቫይረስ አለብህ በሚል ጥርጣሬ ተደብድቦ ተገደለ

ኬንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ይዞታል ብለው የጠረጠሩትን አንድ ግለሰብ ደብድበው መግደላቸውን የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ አስታወቀ።

የፖሊስ አዛዡ ነህሚያ ቢቶክ እንዳሉት እስካሁን በግለሰቡ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የሌለ ሲሆን ምርመራ ግን እየተካሄደ ነው።

ግድያው የተፈፀመው በኬንያዋ ክዋሌ ግዛት በአሳ ምርት በምትታወቀውና ምሳምብዌኒ በተባለች መንደር ነው። ቦታው በባህር ዳርቻውና በነጭ አሸዋው ውበት በቱሪስቶችም በእጅጉ የሚዘወተር ነው።

ግለሰቡ የተገደለው ማክሰኞ ምሽት ሶስት ሰዓት ገደማ ወደ ቤቱ በማምራት ላይ ሳለ እንደሆነ ተገልጿል።

የኬንያ መንግሥት እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሰባት ደርሷል።

መንግሥት ወደ ኬንያ የሚገቡ የውጭ አገር ዜጎች ላይ ጥብቅ የጉዞ እገዳ የጣለ ሲሆን የትምህርት ተቋማትን ዘግቷል፤ ህዝባዊ ስብሰባዎችንም አግዷል።

ኮሮና