በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት የዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የቀብር ሥነ ሥርዓት ውስን ሰዎች በሚገኙበት ሰኞ ይፈጸማል

የፎቶው ባለመብት, Hamlin foundation
ትናንት ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ እንደሚፈጸም ተነገረ።
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ማናጀር ዶ/ር ተሾመ ታፈሰ ለቢቢሲ እንደገለጹት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሰኞ ቀትር 7 ሰዓት ላይ በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።
ዶ/ር ተሾመ እንደተናገሩት ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አድናቂዎቻቸው፣ ደጋፊዎቻቸውና ከየማዕከላቱ የመጡ ሠራተኞች እየተገኙ የስንብት ፕሮግራም ይካሄዳል።
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሕዝብ ስብሰባዎችን መቀነስ ተገቢ ስለሆነም በሚደረገው የስንብትና የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ላይ በአንድ ግዜ የሚገኙ የሰዎች ቁጥር ውስን እንዲሆን እንደሚደረግ ዶ/ር ተሾመ አክለዋል።
ዶ/ር ካትሪንን "የእናቶች እናት ናቸው" ሲሉ የሚገልጿቸው ዶ/ር ተሾመ፤ "የፊስቱላ ችግር እንደነበረ ባልታወቀበት ሰዓት መጥተው ነው፤ ከ60 ሺህ በላይ እናቶችንና ወጣት ሴቶችን ጤንነትን የመለሱ ሴት ናቸው" ብለዋል።
ከአጠቃላይ የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች መካከል አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩት ወደ 160 የሚሆኑት ሠራተኞች የቀድሞ ፊስቱላ ታካሚ የነበሩና ሕይታቸውን አሻሽለው ተቀጥረው የሚሠሩ መሆናቸውን ዶ/ር ተሾመ አስታውሰዋል።
ለሦስት ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለ61 ዓመታት ስለመኖሩት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የህይወት ታሪክ ለማንበብ ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።








