የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ ቡድን ምን እየሰራ ነው?

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰማሉ። ከእነዚህም መካከል የነጻ የስልክ ጥሪ አገልግሎት፣ በአየር ማረፊያ የሚደረገው ምርመራ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና የውሃ አቅርቦት ችግርን የተመለከቱ ጉዳዮች ይነሳሉ።

ይህንን በተመለከተ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] የቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር።

በሽታውን በተመለከተ መረጃ ለመስጠት የተዘጋጀው ነጻ የጥሪ ማዕከል 8335 ላይ በርካታ ሰዎች በመደወል መረጃ ለማግኘትና መረጃ ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም አፋጣኝና አጥጋቢ ምላሽ እየሰጠ አይደለም የሚል ቅሬታዎችን እያሰሙ ነው።

ይህንን በተመለከተ አቶ ዘውዱ በሰጡት ምላሽ በሽታው የሚያሳየው ምልክት የጉንፋን ዓይነት ስለሆነ ብዙ ሰዎች ሪፖርት እንደሚያደርጉና ይህ ደግሞ ካለው የሰው ኃይልና በተጠንቀቅ ላይ ካሉ የአምቡላንሶች ቁጥር አንፃር ከፍተኛ የሚባል እንደሆነም ያመለክታሉ።

ጨምረውም በብሔራዊ ደረጃ ላለው ችግር ምላሽ ለመስጠት ያሉት አምቡላንሶችን ከሦስት ወደ ዘጠኝ እንዲያድግና ከሰው ኃይል አንጻርም ቡድኑም ሃያ እንዲሆን መደረጉን ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት "በአዲስ አበባ ደረጃም የአምቡላንሶችን ቁጥር ከሁለት ወደ አስር እንዲያድግ ተደርጓል። ይህም ሆኖ ግን በ8335 የሚደርሱንን ጥቆማዎች ሁሉ ለመድረስ አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።

ለጤና ተቋማት ሰፊው ህዝብ ከሚጠቀምበት መስመር የተለየ ሁለት የውስጥ መስመሮች መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት አቶ ዘውዱ፤ ከግለሰቦች እንዲሁም ከጤና ተቋማት የሚደርሷቸው ጥቆማዎች ካለው አቅም በላይ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከዱባይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ አዲስ አበባ የገባች አንዲት እንግሊዛዊት ዲፕሎማት በኮሮናቫይረስ መያዟን ተከትሎ በአውሮፕላን ማረፊያው የሚደረግ የሙቀት ልኬት አስተማማኝነት ላይ ጥያቄን አስነስቷል።

ይህንን በተመለከተ አቶ ዘውዱ ሲናገሩ በየትኛውም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ትኩሳት የሌላቸው መንገደኞች ምንም ሳይታይባቸው ማለፋቸው እርግጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"ትኩሳት የሌለው ሰው የሙቀት ልየታውን የማለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፤ ይህም በተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በሚያርፍበት ጊዜ ሙቀት ላይኖረው ይችላል፤ በተጨማሪም ትኩሳትን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን በመውሰድም የማለፍ እድሉም ከፍተኛ ይሆናል" ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት መንገደኞች ከየትኛው አገር ነው የመጡት፣ ከዚያም ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉም ይሁን ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱ እነሱን መከታተል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ተናገረው፤ ከዚህ አኳያም አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ከበሽታው ስጋት አንጻር ሰዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብልን ማድረግ የለባቸውም ብለው የሚያምኑት ባለሙያው አቶ ዘውዱ ይልቁንም ኅብረተሰቡ የፊት ጭንብል እንዲሁም እጅን ከተህዋሲያን የሚያጸዳ ፈሳሽ [ሳኒታይዘር] ለመግዛት በየቦታው የሚያደርገው ከፍተኛ ግፊያና ግርግርን ሥርዓት ለማስያዝም ቡድናቸው እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።

ጨምረውም የበሽታው ክስተት እየተሰጠ ያለው መረጃ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደመሆኑ፤ በጤና ተቋማት የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦች ቶሎ ተግባራዊ ሲሆኑ ባይታይም በሂደት ግን የሚሰጡት መረጃዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ሊሰርፅ እንደሚችልና በቀላሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከውሃ እጥረት እንዲሁም ከትራንስፖርት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችና የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ጀምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በመከላከል ሥራው ባለድርሻ እንዲሆኑና መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ተግባራዊ እንዲደረጉ እየተሰራ መሆኑን አቶ ዘውዱ አሰፋ አመልክተዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያስፈልገው ማን ነው?