ለሦስት ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው 61 ዓመት የኖሩት ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Hamlin foundation
ሥራቸው እንጅ ሌላኛው የሕይወታቸው ገጽታ ብዙም የማይወራላቸው ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን በ96 ዓመታቸው በትናንትናው ዕለት አርፈዋል።
ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን፤ በፈረንጆቹ ጥር 24፡ 1924 ነበር የተወለዱት። አውስትራሊያ የተወለዱት ዶ/ር ካትሪን የማሕጸን ሃኪም ናቸው። ኒውዚላንድ የተወለዱት ባለቤታቸው ዶ/ር ሬጊናልድ ሃምሊንም ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ነበሩ።
ካትሪን ሃምሊን ከሲድኒ ወጣ ባለች አነስተኛ ከተማ ያደጉ ሲሆን በፈረንጆቹ 1946 ከሲዲኒ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ሳይንስ ተመርቀዋል።
በ1958(እ.አ.አ) የኢትዮጵያ መንግሥት አዋላጅ ሃኪሞችን በአዲስ አበባ ልዕልተ ፀሐይ ሆስፒታል ለመቅጠር ያወጣውን ማስታወቂያ ሰምተው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ወሰኑ።
በዓመቱ በ1959 የስድስት ዓመት ልጃቸውን ሪቻርድን ይዘው ሃኪሞቹ ባልና ሚስቶች ውቅያኖስ አቋርጠው አዲስ አበባ ገቡ።

የፎቶው ባለመብት, Hamlin foundation
ካትሪን ሃምሊንና ባለቤታቸው ሬግ ሃምሊን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት እነሆ 60 ዓመታት ተቆጠሩ። በዚያን ወቅት ታዲያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እቅዳቸው ለሦስት ሳምንታት ብቻ ቆይተው ወደሃገራቸው በመመለስ የቀድሞ ሥራቸውን ማሳለጥ ነበር።
በዚያች ገና የኢትዮጵያን መሬት በረገጡባት ምሽት ግን አንድ የማሕጸን ሃኪም "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፊስቱላ ሁኔታ ልባችሁን ይሰብረዋል" ሲል ነገራቸው።
በዚያን ወቅት ታዲያ እነ ሃምሊን የፊስቱላን በሽታ አይተው አያውቁም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የማሕጸን ፊስቱላ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ጠፍቶ ለዚሁ ተግባር ተብለው የተሰሩ ሆስፒታሎችም ተዘግተው ነበርና ነው።
ኒዮርክን የመሳሰሉት ትልልቅ ከተሞችም በሽታውን አጥፍተው ገና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ነበር የፊስቱላ ሆስፒታሎቻቸውን የዘጋጉት።
በዚህ ነበራዊ ሁኔታ ውስጥ የኖሩት እነ ካትሪን ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ በሽታ ምንም አይነት ህክምና እንደሌለውና በርካቶችን እያሰቃየ እንደሆነ እውቀቱ አልነበራቸውም።
ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነባራዊ ሁኔታውን ማየት ሲችሉ ግን ተገረሙ። በእርግጥም ያ የማሕጸን ሃኪም እንደነገራቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያጋጥመው ፈውስ አልባ የሴቶች የፊስቱላ በሽታ የነካትሪን ልብ ተሰበረ።
ለሦስት ሳምንታት የተባለው የኢትዮጵያ ቆይታ ተሰርዞ ተጨማሪ ወራትን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማሳለፍ ወሰኑ። ምክንያታቸው ደግሞ በፊስቱላ የሚሰቃዩ የኢትዮጵያዊያን እንስቶችን እንባ ማበስና ከስቃያቸው መገላገል ነበር።
እነዚህ ሁለት የቀዶ ሕክምና ሙያተኞች ታዲያ ለሦስት ሳምንታት የመጡበትን የኢትዮጵያ ቆይታ በማራዘም በፊስቱላ ምክንያት የሚገለሉትን ኢትዮጵያዊያን ለሦስት ዓመታት ለማከም ወስነው ወደ ሥራ ገቡ።
ሥራቸው ፈጣን ለውጥ አስመዘገበ። በተለይ በወሊድ ጊዜ የሚከሰተው የማሕጸን ፊስቱላ ታማሚዎችን ከማሰቃየቱ በላይ በማሕበረሰቡ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታዩ የሚያደርግና መገለልን የሚያስከትል ነበር።
ሶስት ዓመት ሲሞላቸው ግን አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች በመገኘታቸው ወደ አውስትራሊያ ከመመለስ ይልቅ በዚሁ ሥራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠል እንዳለባቸው ባልና ሚስቱ ወሰኑ። ለሥራቸው እንዲያግዛቸው አንድ የሕክምና ተቋም ማቋቋም ደግሞ ተከታዩ እቅዳቸው ነበር።
እናም ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በአስራ አምስተኛው ዓመታቸው አዲስ አበባ ውስጥ በ1974 (እ.አ.አ) የፊስቱላ ማዕከል የሆነ ሆስፒታል ሠሩ።
ይህ ሆስፒታልም ከ45 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ከህመም ፈውሶ መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Hamlin foundation
ዛሬ የኢትዮጵያ ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል የማሕጸን ፊስቱላን ለማጥፋት በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርአያነት የሚታይ ተቋም ነው። በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ ሙከራዎችን አድርጎ ሴቶችን ከሕመማቸው ፈውሶ፤ ወደ ትክክለኛ የሕይወት መስመራቸው የሚያስገባና በቤተሰባቸውና በማሕበረሰባቸው ያላቸውን ሚና እንዲያስቀጥሉ የሚያስችል ተቋም ሆኗል።
የእርሳቸው [ዶ/ር ካትሪን] ፋውንዴሽን፤ 'ካትሪን ሃምሊን ፋውንዴሽን' አንድ ዓላማ ብቻ ሰንቋል፤ ብቸኛ ዓላማውም ፊስቱላን ከምድረገጽ ማጥፋት ነው።
ይህ የእርሳቸው ተቋም አቅም የሌላቸው የፊስቱላ ታማሚ ሴቶችን በነጻ የሚያክም ተቋም ነው። ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ላደረጉት መተኪያ የሌለው አስተዋጽኦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ሰጥቷቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hamlin foundation
ለሦስት ሳምንታት ሥራ ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን፤ የፊስቱላ ታማሚ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ስቃይ ቀሪ የግል ሕይወታቸውን አስረስቶ የበጎ አድራጎት ሥራቸውን ብቻ ለ60 ዓመታት እንዲሰሩ አድርጓቸዋል።
በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያን አገራቸው አድርገው ላለፉት 60 ዓመታት ከሞት ጋር የሚታገሉ የፊስቱላ ታካሚዎችን ወደ ሕይዎት እየመለሱ የሙያና የሞራል ግዴታቸውን ማድረግ ከሚችሉት በላይ ሲከፍሉ ከቆዩ በኋላ፤ ዶክተር ካትሪን ሃምሊን አዲስ አበባ ውስጥ በአስገነቡት የፊስቱላ የሕክምና ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ በ96 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።













