የሩሲያ ወታደሮች ሰቨሮዶነስክ ከተማን ለመያዝ ተቃርበዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ወራትን ባስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወደ ሰቨሮዶንስክ ከተማ የሚወስደውን አውራ ጎዳና ለመቆጣጠር ኃያል ጦርነት እየተደረገ ነው።
ሩሲያ ይህን ከተማ ለመቆጣጠር ተቃርቢያለሁ ብትልም አንድ ከፍተኛ የዩክሬን ባለሥልጣን ነገሩን አስተባብለዋል።
ይህ ጎዳና ዩክሬን የምትቆጣጠራቸውን ከተሞች ሩሲያ ከያዘቻቸው ከተሞች ጋር የሚያገናኝ ከፍ ያለ ወታደራዊ ዋጋ ያለው ነው።
"ሉሃንስክ አልተቆረጠችም" ብለዋል ሰርሂይ ሃይዳይ የተባሉ የዩክሬን ወታደራዊ ባለሥልጣን።
አሁን ጦርነቱ እየተደረገ ያለው በምሥራቁ ክፍል ሰቨሮደንስክ ከተማ አቅራቢያ ነው።
ከተማዋን ለመቆጣጠር ታዲያ የባክሙት አውራ ጎዳናን መያዝ በቂ ነው።
ጦርነቱ ያየለውም ለዚሁ ነው።
እኚሁ የዩክሬን ባለሥልጣናት ይህን ቁልፍ መንገድ ለመያዝ ከፍ ያለ ጦርነት እየተካሄደ እንደሆነ ግን አልሸሸጉም።
ሰቨሮዶንስክ በቀን ለ24 ሰዓት በአየርና በምድር ኃይል እየተደበደበች ትገኛለች። ማክሰኞ ዕለት በነበረ ጥቃት 6 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
ሩሲያ ከዚች ከተማ ቅርብ ያለችውን ሊቻንስክ ከተማን ከተቆጣጠረች ሙሉ የሉሃንስክ ከተማን በእጇ ታስገባለች ተብሎ ይጠበቃል።
የሉሃንስክ አካባቢ አስተዳዳሪ የሩሲያ ወታደሮች ንጹሃንን ዒላማ አድርገዋል ሲሉ ይከሳሉ።
በሰቨሮዴንስክ ብቻ 15ሺህ ነዋሪዎች በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።
"ከተማዋን መቆጣጠር ሲያቅታቸው ከተማዋን ማጥፋትን መረጡ" ሲሉም ከሰዋል አስተዳዳሪው።
ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከከፈተች ሦስት ወራት ቢያልፍም ፈጣን ድል አልቀናትም።
የብዙ ወታደራዊ ተንታኞች ግምት ሩሲያ የምትፈልጋቸውን ግዛቶች በአጭር ጊዜ እጇ ከማስገባት የሚያቆማት ኃይል የለም የሚል ነበር።
ለሩሲያ ግስጋሴ መገታት አንዱና ዋንኛው ምክንያት የሩሲያ ወታደሮች የመዋጋት ፍላጎት ዝቅተኛ መሆንና በተቃራኒው የዩክሬን ወታደሮች በከፍተኛ ወኔ እየተዋጉ በመሆኑ ነው ይላሉ ተንታኞች።
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ አቅራቢያ ከበባ በመፈጸም በመጀመርያዎቹ የጦርነቱ ሳምንታት ፈጣን ድል ታደርጋለች ተብሎ ሲጠበቅ ነው ጦርነቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ምሥራቁ ክፍል ለማድረግ ከሰሜንና ምዕራብ ዩክሬን ያፈገፈገችው።
በዚህ ጦርነት ሩሲያ በሺህ የሚቆጠሩ ታንኮችና ወታደሮችን እንዳጣች እየተነገረ ነው።
የሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቪዠን ትናንት ለመጀመርያ ጊዜ ቪላድሚር ፑቲን ሞስኮ ሆስፒታል ሄደው የቆሰሉ ወታደሮችን ሲያነጋግሩ አሳይቷል።
በዚህ ለአጭር ሰዓት በቆየው ተንቀሳቃሽ ምሥል ፑቲን ለአንድ የቆሰለ ወታደር "አባትህ ባንተ ይኮራል" ሲሉ ይሰማል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው በምሥራቅ ዩክሬን ሁኔታዎች እጅግ እየከፉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ ትኩረቷን ሙሉ በሙሉ ወደ ምሥራቅ ብታደርግም ከትናንት በስቲያ ከባድ የተባለ የሚሳኤል ጥቃት ወደ ደቡባዊቷ ከተማ ዛፖሪሽያ አስወንጭፋለች።
ከ60 በላይ ቤቶችና የገበያ ማዕከላትንም አውድማለች።
ቪላድሚር ፑቲን፣ ሩሲያ አሁን ከዩክሬን በያዘቻቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የሩሲያን ፓስፖርት በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ አጽድቀዋል።
ይህም ሩሲያ በረዥም ጊዜ ዩክሬንን ለማጠቃለል ያላትን ትልም ያሳበቀ ሆኗል።
በ2014 ከሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ዶኔስክ እና ሉሃንስክ አካባቢዎች ራሳቸውን የሩሲያ ሪፐብሊክ አድርገው ነው የሚመለከቱት።
ሩሲያ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ስምንት መቶ ሺህ ነዋሪዎች ፓስፖርት አድላለች።












