በቴክሳስ የተገደለችው መምህርት ባለቤት 'በሀዘን' ሕይወቱ አለፈ

በቴክሳስ፣ ኡቫልዴ በርካቶች በተገደሉበት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ የተቀመጡ አበባዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቴክሳስ፣ ኡቫልዴ በርካቶች በተገደሉበት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ የተቀመጡ አበባዎች

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት፣ ዩቫልዴ ማክሰኞ ዕለት በተፈፀመው የጅምላ ጥቃት ከተገደሉት መምህራን መካከል የአንዷ ባለቤት በልብ ህመም ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።

ጆ ጋርሺያ በሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ23 ዓመታት ያስተማረችው ኢርማ ጋርሺያ ባለቤት ነበር።

ኢርማ 19 ህጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎች በተገደሉበትና መሣሪያ የታጠቀው ወጣት በከፈተው ተኩስ ከተገደሉ መምህራን አንዷ ነበረች።

ለ24 ዓመታት በትዳር የቆዩት ጥንዶቹ አራት ልጆችን አፍርተዋል።

ሐሙስ ምሽት በኢንተርኔት አማካይነት በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስነ-ስርዓት ለኢርማ ቤተሰቦች መጀመሪያ ላይ ይሰበሰባል ተብሎ ከተቀመጠው 10 ሺህ ዶላር ግብ፣ 1.6 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቧል።

በ 'ጎ ፈንድ ሚ' ገጽ ላይ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሂደት የተጀመረው በኢርማ ዘመድ ደብራ ኦስቲን መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በገጹም ላይ "ጆ በባለቤቱ ሞት ልቡ በመሰበሩ ሕይወቱ ማለፉን አምናለሁ" ስትል የሞቱ ምክንያት የሚስቱ ሀዘን መሆኑን ጽፋለች።

የኢርማ የወንድም ልጅ ጆን ማርቲኔዝም በትዊተር ገጹ "ጆ በተገደለችው ሚስቱ ሀዘን ምክንያት ሕይወቱ አልፏል" ብሏል።

በአካባቢው የፎክስ ተባባሪ ሚዲያ ጆ በልብ ህመም ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን ዘግቧል።

ጆ እና ኢርማ ጋርሺያ
የምስሉ መግለጫ, ጆ እና ኢርማ ጋርሺያ

ጥንዶቹ ይህችን ዓለም የተሰናበቱት እድሜያቸው በ12 እና በ23 መካከል የሚገኝ ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ ልጆቻቸውን ትተው ነው።

በዩቫልዴ በርካቶች የተገደሉበትን ተኩስ ተከትሎ የኢርማ የወንድም ልጅ፣ ማርቲኔዝ፣ ኢርማ እስከ መጨረሻ እስትንፋሷ ድረስ ህጻናትን በእቅፏ ይዛ በፖሊስ መኮንኖች መገኘቷን ለኒዮ ርክ ታይምስ ተናግሯል።

"በክፍሏ ያሉ ህጻናትን ለመጠበቅ ስትል የራሷን ሕይወት መስዋዕት አድርጋለች፤ ኢርማ ጀግና ናት" ሲል ማርቲኔዝ በገንዘብ ማሳባሰቢያ ገጹ ላይ ጽፏል።

በተኩሱ የተገደሉት ኢርማ እና ሌላኛዋ መምህርት ኢቫ ማርለስ ለ5 ዓመታት ያህል አብረው አስተምረዋል። ከ40 ዓመታትም በላይ ልምድ የነበራቸው ናቸው።