ናይጄሪያ የሕፃናት ወሲብ ቪድዮ የሚያጋሩ ሰዎችን በ14 ዓመት እሥር ልትቀጣ ነው

ስልክ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የናይጄሪያዋ ትለቋ ከተማ ሌጎስ አስተዳዳሪዎች የሕፃናት ወሲብ የሚታይባቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የሚያጋሩ ሰዎችን በእስራት ሊቀጡ ነው።

ማንኛውም ዓይነት የሕፃናት ወሲብን የሚያሳይ ምስል የሚያጋሩ አሊያም የሚቀበሉ ሰዎች የ14 ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎችን ይህን አዲስ ሕግ ያወጡት አንዲት ታዳጊ ወሲባዊ ጥቃት ሲደርስባት የሚያሳይ ምስል በማሕበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው።

ታዳጊዋና የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ባለፈው መጋቢት በስፖርታዊ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ወደ ዱባይ ባቀኑበት ወቅት ነው ይህ ክስተት ያጋጠመው።

ወደ ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ በትምህርት ቤት በኩል ያቀናችው የ10 ዓመቷ ታዳጊ ጥቃት ሲደርስባት የሚያሳየው ምስል ብዙዎች ተጋርተውታል።

የታዳጊዋ እናት ልጃቸው በወንድ ተማሪ ተመርዛ ነው ጥቃት የደረሰባት ይላሉ።

እናት የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ክስተቱን ለመሸፋፈን ሞክረዋል ሲሉ ይከሳሉ።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሕፃናቱ ወደ ዱባይ ያቀኑት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከመጋቢት 10-13 በነበረው የትምህርት ቤቶች ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ ነው ሲሉ ዘግበዋል።

የሌጎስ ግዛት አስተዳደር ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ትምህርት ቤቱ ወንዱን ተማሪ እንዳገደው ገልጦ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

ከዚህ ክስተት በኋላ ነው የሌጎስ አስተዳደር የሕፃናት ወሲብ የሚንፀባረቅበት ምስልን የተጋራ ወይም ያጋራ በሕግ ይቀጣል ያለው።

ይህ አነጋጋሪ ክስተት ተከትሎ በርካታ ናይጄሪያዊያን በማሕበራዊ ድር አምባዎች ድርጊቱን ተቃውመውታል።