በፊሊፒንስ አውሎ ንፋስ ባስከተለው የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ 167 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፊሊፒንስ ከቀናት በፊት ትሮፒካል የሚል መጠሪያ ያለው አውሎ ንፋስ ተቀስቅሶ ባስከለው የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ ቢያንስ 167 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
በተጨማሪም 110 ሰዎች የገቡበት እንዳልታወቀ እና 1.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን የአገሪቱ የአደጋ ምላሽ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በማዕከላዊ ለይቲ አውራጃ ውስጥ በባይባይ ከተማ ዙሪያ ያሉ መንደሮች በዚህ ተፈጥሯዊ አደጋ ክፉኛ የተመቱ ሲሆን በወንዞች ሙላት ምክንያት በውሃ ተጥለቅልቀዋል።
ፒላር በተባለ አንድ መንደር ውስጥ ያሉ 80 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በውሃ ተውጠው ነበር። ኤጀንሲው በአገሪቱ በደቡብ እና በማዕከላዊ ክፍሎች ሞት መመዝገቡንም አሳውቋል።
የአካባቢው ሰዎች አጋቶን በሚል የሚጠሩት አውሎ ንፋስ በሰዐት 65 ኪሎ ሜትር የሚከንፍ ነው።
በዚህም ምክንያት አውሎ ንፋሱ በሚከሰትበት ወቅት ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ መጠለያዎች ወይም ከፍታ ወዳላቸው ስፍራዎች ይሸሻሉ።
ምንም እንኳን ማክሰኞ ዕለት ችግሩ ቢቃለልም የነፍስ አድን ሥራው ግን በዝናብ ምክንያት ተስተጓጉሏል።
ይህ አውሎ ንፋስ በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ሲሆን እንዲህ ያለ አውሎ ንፋስ በፊሊፒንስ በየዓመቱ በአማካይ እስከ 20 ጊዜ ይከሰታል።
ከቀናት በፊት የተነሳው ይህ አውሎ ንፋስ የተከሰተው፣ ከአራት ወራት በፊት የአገሪቱን ደቡብ ምሥራቅ ደሴቶችን ያወደመ ሌላ አውሎ ንፋስ 375 ሰዎችን ከገደለ እና 500 ሺህ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ነው።
ያ አውሎ ንፋስ በዚያ ዓመት በፊሊፒንስ እጅግ የጠነከረ እና አስከፊው የተባለ ሲሆን ባለሙያዎች የንፋሱ ፍጥነት ከተጠበቀው በላይ ብርቱ ነበር ብለዋል።
ፊሊፒንስ ባለችበት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት ለአየር ንብረት አደጋዎች በጣም ተጋላጭ ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ ስትሆን ተደጋጋሚ አደጋዎችንም አስተናግዳለች።

የፎቶው ባለመብት, AS YOU WISH PHOTOGRAPHY












