አሠልጣኝ ኤሪክሰንን ጨምሮ ታዋቂ ተጫዋቾችን ያጭበረበረው ደላላ

የፎቶው ባለመብት, Nottingham Post
ለእግር ኳስ ደጋፊዎች እንደ መጀመሪያዋ የውድድር ዘመን ጨዋታ ጣፋጭ የለም።
በጉጉት የጠበቁት ሊግ አሊያም የዋንጫ ፍልሚያ ሲጀምር የምትታየው የመጀመሪያዋ ጨዋታ እንደ ጨቅላ የሚያስቦርቅ ነገር አላት።
ጊዜው 2009 በፈረንጆቹ። በእንግሊዝ ሊግ ሁለት የሚጫወተው ኖትስ ካውንቲ የ09/10 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ጨዋታውን እያካሄደ ነው።
ኖትስ ካውንቲ ከዚህ ጨዋታ አንድ ወር ቀድሞ ሙንቶ ፋይናንስ በሚባል ጥምር ተቋም ተገዝቷል።
ሙንቶ፤ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኖትስ ካውንቲን ከፕሪሚዬር ሊጉ ዝቅ ብሎ ለሚደረው የቻምፒዮንሺፕ ውድድር ለማድረስ ቃል ገብቷል።
እኔን ጨምሮ የዕድሜ መሰሎቼ ወጣት የኖትስ ደጋፊዎች የከተማ ተቀናቃኛችን ኖቲንግሃም ፎረስትን ጥለን ወደላይኛው ሊግ ስናል እያለምን ነው።
ነገር ግን ነባር የቡድኑ ደጋፊዎች ይህ የአዲሱ የክለቡ ባለቤት ቃል ብዙም የተዋጠላቸው አይመስልም።
ከጥቂት ቀናት በኋላ እውቁ አሠልጣኝ ስቬን-ጎራን ኤሪክሰን የክለቡ ዳይሬክተር ሆነው ተቀጠሩ።
እንግሊዝን ለዓለምና አውሮፓ ዋንጫ ያደረሱት አሠልጣኝ ካሜራው መብራቱን እየለቀቀባቸው ለዓለም ሕዝብ ስለክለቡ መግለጫ ሰጡ።
ይሄኔ የክለቡ ጥንታዊ ደጋፊዎች ሳይቀሩ ሕልማቸው ለመለመ። ኖትስ ካውንቲ አይደለም ለቻምፒዮን ሺፕ ለፕሪሚዬር ሊግ የመወዳደር አቅም አለው ሲሉ ይፎክሩ ጀመር።
አዎ፤ የምናወራው ከሊግ 2 ላለመውረድ ስለሚታገለው፤ የደረጃ ሠንጠረዡ አጋማሽ ለመድረስ ስለሚንጠራራው ኖትስ ካውንቲ ነው።
እነሆ ኖትስ ካውንቲ በኤሪክሰን እየተመራ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ሊገሰግስ ነው።
9 ሺህ ሰው የሚያስተናግደው ሜዶው ሌን ጠጠር ቢወረወር መሬት እንዳያደርፍ ሆኖ ሞልቷል።
ኤሪክሰን በተዘጋጀለቻው የክብር መንበር ተሰይመው ቡድናቸውን ይመለከታሉ። አዲሱ ፈራሚ ሊ ሂዩስ ብቃቱን ለማሳየት ቋምጧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኖትስ ካውንቲ ከብራድፈርድ ሲቲ። ጨዋታው ተጀመረ። የመጀመሪያው ጎል - ኖትስ ካውንቲ። ስታድየሙ በአንድ እግሩ ቆመ።
ሊ ሂዩስ ጎል አገባ። ደገመ። ደጋገመ። በመጀመሪያ ጨዋታ ሶስታ [ሃትሪክ] ሠራ።
ፍልሚያው በኖትስ ካውንቲ 5 ለምንም አሸናፊነት ተጠቀቀ።
በኖትስ ካውንቲ ደጋፊነቴ ከተደስትኩባቸው ቀናት መካከል ይህ ከቤተሰቦቼ ጋር ያየሁት ፍልሚያ በፍፁም ከአእምሮዬ አይጠፋም።
ነገር ግን ሁሉም ነገር ሕልም ነበር።
ምንም እንኳ የዛኔ ነገሩ ባይገባኝም ከመካከለኛው ምስራቅ ናቸው የተባሉት ቱጃር የክለቡ ባለቤቶች ሐሰት ነበሩ።
ባለቤቶቹ ካዝና ውስጥ አሉ የተባሉት ሚሊዮኖች ረብጣዎች የውሃ ሽታ ሆኑ። የደጋፊዎች ሕልም መክኖ ቀረ።
ክለቡ፣ ደጋፊዎቹ እንዲሁም ኤሪክሰን የአጭበርባሪው ረስል ኪንግ የቅጥፈት ስልት ሰለባ ሆኑ።
እነሆ ይህ ከሆነ ከአስር ዓመት በኋላ እኔና ሌሎቹ የሙያ አጋሮቼ ምንድነው የተፈጠረው የሚለውን ለመመርመር ተነሳን።
ያገኘነውን ነገር ግን ካሰብነውም በላይ ውስብስብ ነው። ዓመታት የወሰደ፤ ከኖቲንግሃም በጀርዚ አድርወጎ ባህሬይንን ተሻግሮ በዱባይ በኩል ሰሜን ኮሪያ የዘለቀ የሐሰት፣ ስግብግብነት ታሪክ።
ደጋፊዎቹ ክለቡ ሲሸጥ ባለቤቱ ማነው ከየትስ ነው የመጣው፤ ሚሊዮን ዶላሮቹስ የማናቸው፤ ብለው አልጠየቁም።
ይባስ ብሎ ኤሪክሰን የክለቡ የእግር ኳስ ዳይሬክተር ሆነው ሲፈርሙ ሁሉም ጮቤ ረገጠ።
ስዊድናዊው አሠልጣኝ ቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገቡት። ጊዜ ሳይፈጁ ተጫዋቾች ማስፈረም ጀመሩ። አንድ ካስፐር ሽማይክል የሚባል ወጣትና ተስፈኛ ግብ ጠባቂ ለማምጣት እንዳቀዱም ተናገሩ።
ሽማይክል ሊድስ ዩናይትድን ከመቀላቀሉ በፊት ለኖትስ ካውንቲ አንድ ዓመት ተጫውቷል።
ኤሪክሰን ወደ ኖትስ ካውንቲ ከመምጣታቸው በፊት ማንቸስተር ሲቲን አሠልጥነዋል። ይሄኔ ነው የዝነኛው ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል ልጅ ካስፐር ሽማይክልን የተመለከቱት።
ካስፐር በወቅቱ እንደአሞራ ተወርውሮ ኳስ የሚቀልበው ጆ ሃርትን ረትቶ ቋሚ ተሰላፊ መሆን ባለመቻሉ ወደሌላ ክለብ መዛወርን ያልማል።
ኤሪክሰን ካስፐርና አባቱን ፒተር ሽማይክልን ካሳመኑ በኋላ ዓመታዊ ደሞዝ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ እንዲባለ አስማምተው ለአምስት ዓመት አስፈረሙት።
ምን ሽማይክል ብቻ ኖትስ ካውንቲ ማስፈረም የማይችለው እግር ኳሰኛ እንደሌለ ይወራ ጀመር።
ብራዚላዊው ተከላካይ ሮቤርቶ ካርሎስ፤ ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሉዊዝ ፊጎ የጡረታ ዘመናቸውን በኖትስ ካውንቲ ሊያሳልፉ ይችላሉ የሚሉ ወሬዎች ይናፈሱ ጀመር።
ነገር ግን የብዙዎችን ቀልብ ገዝቶ የነበረው የ34 ዓመቱ እንግሊዛዊ ዴቪድ ቤካም ኤልኤ ጋላክሲን ጥሎ ሊመጣ ነው የሚለው የከተማው ወሬ ነበር።
በዚህ ሁሉ ወሬ መሃል የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ካያቸው ድንቅ ተከላካዮች መካከል አንዱ ሆነው የ34 ዓመቱ ሶል ካምፕቤል ወደ ሜዶው ሌን ዘለቀ።
ካምፕቤል ከአንድ ወር በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሞርካምቤ ጋር በነበረው ፍልሚያ አደረገ።
ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ተፋላሚዎቻችን ሜዳ ሄደን ጨዋታውን ተመለከትን። ውጤቱ ግን አስካፊ ነበር። ኖትስ ካውንቲ 2-1 ተረታ።
ደጋፊዎች መቸም ሽንፈት ያለ ነው፤ ካምፕቤልን ወደ አቋሙ መመለሱ አይቀሬ ነው ብለው ተስፋ ሰንቀው ወደ ቤታቸው ገቡ።
ቢሆንም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሶል ካምፕቤል ከኖትስ ጋር ያለውን ስምምነት አፍርሶ መልቀቁ ተሰማ።
ይህ ዜና ከመሰማቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ዘ ሰን የተባለው ጋዜጣ ኖትስ ካውንቲን የደለለው ረስል ኪንግ የተባለው ግለሰብ በ1990ዎቹ በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ ሁለት ዓመት ከርቸሌ ከርሞ እንደወጣ አስነበበ።
ክለቡ፤ ኪንግ "ስትራቴጂያዊ አማካሪ" ነው እንጂ ከዚያ ዘለለ ሚና የለውም ሲል ዘገባውን አጣጣለ።
ነገር ግን እውነታው ይህ አልነበረም።
ኪንግ፤ የባህሬይን ንጉሣዊ ቤተሰብ የውጭ ሃብት ተቆጣጣሪ ነኝ በማለት ከለንደን ኢንቨስትመን ባንክን ያታልል ኖሯል።
ረስል ኪንግ ከዚሁ ባንክ ማረጋገጫ አስፅፎ ነው የኖትስ ካውንቲ ባለቤትነቱን ያረጋገጠው።
በተመሳሳይ ሰዓት የአንድ ግዙፍ የማዕድን አውጭ ኩባንያ ባለቤት ነኝ በማለት ከሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጋር የድንጋይ ከሰልና ወርቅ ለማውጣት ስምምነት ይገባል።
ይሄን የምርመራ ዘገባ ስናዋቅር ያገኘናቸው ኤሪክሰን ግለሰቡ አግባብቶ ወደ ሰሜን ኮሪያ እንደወሰዳቸውና የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ለ2010 ዓለም ዋንጫ እንድናልፍ ደካማ ምድብ ውስጥ መድቡን ብለው እንደጠየቋቸው ነግረውናል።
ኤሪክሰን ይህን በፍፁም ማድረግ እንደማይችሉ ለሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት እንደነገራቸው ያክላሉ።
ከሰሜን ኮሪያ ጋር የማዕድን ማውጣት ስምምነት የገባው ኪንግ ይህን ተጠቅሞ ኩባንያው በአክሲዮን ገበያ እንደሚዘገብ መጣር ይጀምራል።
ነገር ግን ይህ አልተሳካለትም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይሄኔ ኪንግ ወደ ባሕሬይን ይበርና በመካከለኛው ምስራቅ እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ያለ ጋዜጣ ለመመሥረት ያቅዳል።
ኪንግ የኋላ ኋላ የማጭበርበር ሂደቱ አልሳካ ብሎት በፖሊስ ይፈለግ ጀመረ። በስተመጨረሻም የካቴና ሲሳይ ሆኖ በአሜሪካዋ ከተማ ጀርዚ በፈፀመው ወንጀል ምክንያት ወደ ከርቸሌ ይላካል።
ሰውየው ባለፈው ዓመት ከእሥር ተለቋል። ስለሰራነው የምርመራ ዘገባ ምላሽ ካለው በሚል ጥያቄ ብናቀርብለትም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በኪንግ ተጭበርብሮ ብሩን ሲዘራ የነበረው ኖትስ ካውንቲ ሁለት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ታሪክ ሆኖ ከመቅረት ተርፎ አሁን በአዲስ ባለቤት እጅ ወድቋል።
እኔን ጨምሮ በርካታ ደጋፊዎች ክለባችን ባለመሸጡ ደስተኛ ብንሆንም ያንን የስድስት ወር የደስታ የሃዘን ጊዜ መቼም አንረሳውም።
ምንድነው የሆነው? ሕልም ነው? ወይስ እውነት?
ኖትስ አሁን በናሽናል ሊግ ውድድር ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።












