ሩሲያ ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያ የሚልኩ ምዕራባውያን አገራት ላይ ዛተች

ዩክሬን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ ምዕራባውያን አገራት ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያ መላክ ካላቆሙ በስተቀር "የእጃቸውን እንደሚያገኙ" ዛተች።

ሩሲያ እርምጃ ለመውሰድ ከዛተችባቸው አገራት አንዷ አሜሪካ ናት።

አሜሪካ ከሰሞኑ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ወደ ዩክሬን እንደሚላኩ አስታውቃ ነበር።

በሌላ በኩል ከቀናት በፊት በጥቁር ባሕር ስለሰመጠው የሩሲያ የጦር መርከብ አሁንም ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዩች አሉ።

ሞስኮ ለመርከቧ መስመጥ ምክንያቱ "ማዕበል መበርታቱ ነው" ብትልም ኪየቭ መርከቡን መታ እንዳሰጠመች ተናግራለች።

አሜሪካ በበኩሏ መርከቡ በሁለት የዩክሬን ሚሳኤሎች ተመቷል ብላለች።

የመርከቡ ካፒቴን መሞቱን ከዩክሬን በኩል መረጃ ቢወጣም አልተረጋገጠም።

በሌላ በኩል የዩክሬን መዲና ኪየቭ ውስጥ ወደ 900 የሚጠጉ የንጹሀን ዜጎች አስክሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

የከተማዋ የፖሊስ ኃላፊ አንድሪ ነቢቶቭ "በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የ900 ንጹሀን ዜጎችን አስክሬን አግኝተን ወደ ተጨማሪ ምርመራ ልከናል" ብለዋል።

ከተገኙት አስክሬኖች መካከል ከ350 በላዩ ቡቻ ከተባለችው ግዛት የተገኙ ናቸው።

በዚህ ግዛት የተፈጸሙት ወንጀሎች ከጦር ወንጀል የሚስተካከሉ ናቸው የሚለውን ክስ ሞስኮ አጣጥላለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ወረራው ከተጀመረ ወዲህ ወደ 3,000 የሚጠጉ ዩክሬናውያን ወታደሮች እንደሞቱና 10,000 የሚደርሱ ደግሞ እንደቆሰሉ ተናግረዋል።

ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ሩሲያ ሚሳኤል ልትተኩስ ትችላለች የሚል ስጋት እንዳለም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊት 1,300 የዩክሬን ወታደሮች እንደሞቱና በሩሲያ ወገን የሞቱት ከዚህ በላይ እንደሆኑ ዘለንስኪ ገልጸው ነበር።

ይህንን የሞቱ ንጹሀን ዜጎችን ያልጨመረ ቁጥር ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን አላጣራም።

ሁለቱም ወገኖች በሌላው ወገን ወታደሮች ላይ የደረሰውን ጉዳት አጋነው ሲናገሩ ተስተውሏል። በሁለቱም በኩል በይፋ የሚነገሩ ቁጥሮች ግን ሌላኛው ወገን ከሚለው ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል።