ሰነድ አልባው ስደተኛ በሎተሪ የወጣለትን 270 ሺህ ዶላር ለማግኘት እየታገለ ነው

አልጄሪያዊው ግለሰብ ባሸነፈው ገንዘብ ቤልጄም ውስጥ ኑሮውን መመሥረት እንደሚፈልግ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, EVN

የምስሉ መግለጫ, አልጄሪያዊው ግለሰብ ባሸነፈው ገንዘብ ቤልጄም ውስጥ ኑሮውን መመሥረት እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ቤልጄም ውስጥ የሚኖረው እና ሰነድ አልባው አልጄራያዊ ግለሰብ ፈጣን ሎተሪ ቆርጦ ያገኘውን 270 ሺህ ዶላር በእጁ ለማስገባት እየጣረ መሆኑ ተሰምቷል።

ሰውዬው ያሸነፈው የገንዘብ መጠን ትልቅ በመሆኑ የሎተሪ አስተዳዳሪው ተቋም በጥሬ ገንዘብ መክፈል ሰለማይችል የግድ የባንክ አካውንት መክፈት ይኖርበታል።

አሸናፊው ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ ወረቀት የለውም።

በሎተሪው ያገኘውን ይህንን ገንዘብ ለመጠየቅ የሞከረ አንድ ጓደኛው በስርቆት ወንጀል ተጠርጥቶ ለአጭር ጊዜ ታስሮ ነበር።

አልጄሪያዊው ግለሰብ ባሸነፈው ገንዘብ ቤልጄም ውስጥ ኑሮውን መመሥረት እንደሚፈልግ ተናግሯል።

"ገንዘቡን ሳገኝ መኖሪያ የሚሆነኝን ቦታ ብራሰልስ ውስጥ እገዛለሁ። መኪናም ልገዛ እችላለሁ" ሲል ማንነቱ ያልተገለጸው የሎተሪ አሸናፊ ለቤልጄም መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

የ28 ዓመቱ አልጄሪያዊ ምንም ዓይነት የመታወቂያ ወረቀትም ሆነ ቋሚ የመኖሪያ ቦታ ስለሌለው ገንዘቡን ለመጠየቅ የሚረዳው የሆነ ዓይነት ማረጋገጫ ያስፈልገዋል።

"ማንነቱን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን እየፈለግን ነው። በአልጄሪያ የሚገኙ ቤተሰቦቹን ማነጋገር ይኖርበታል" ሲሉ ቬርስትሬት የተባሉት ጠበቃው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

የሎተሪ አስተዳደሩ ቃል አቀባይ ግን አሸናፊዎች ምን ዓይነት ሰነድ ማቅረብ እንዳለባቸው በግልጽ አላሳወቁም።

የአሸናፊው ግለሰብ ጓደኛ የሆነ እና ሰነድ ያለው ግለሰብ ብራሰልስ ወደ ሚገኘው የሎተሪ ዋና መሥሪያ ቤት በማቅናት በአሸናፊው ስም ገንዘቡን ለመጠየቀ የሞከረ ቢሆንም ጠያቂው እና ሁለት ጓደኞቹ ለማጨበርበር ሞክራችኋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ሆኖም አሸናፊው ሁኔታውን ካስረዳ በኋላ ተለቀዋል።

አልጄሪያዊው አሸናፊ እንደሆነ የሚያረጋግጠው የሎተሪ ወረቀት ፍርድ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ሲሆን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግለሰቡ የሽልማት ገንዘቡን እስኪያገኝ ድረስ ከአገር ላለመውጣት ቃል መግባታቸውን ጠበቃው ቬርስትሬት ተናግረዋል።

ግለሰቡ ከአራት ወራት በፊት ከአልጄሪያ ተነስቶ በጀልባ ስፔን መድረሱን የቤልጄም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከስፔን በመነሳት በእግሩ እየተጓዘ በፈረንሳይ አድርጎ ቤልጄም መግባቱም ታውቋል።

የመጀመሪያ ሐሳቡ ዩናይትድ ኪንግደም መግባት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሐሳቡን ቀይሮ በቤልጄም መኖር እና ቤተሰብ መመሥረት ይፈልጋል።

"ሚስት እፈልጋለሁ" የሚለው ሰውዬው "የምፈልገው ግን በገንዘቤ ሳይሆን በልቤ ነው" ሲል ተደምጧል።