ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፡ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከዳኝነት ውጭ ግድያ መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, unicef/ethiopia
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24/ 2014 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀሙን ገለጸ።
ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የነበረነረ አሰቃቂ ቪዲዮን ተከትሎ የኢሰመኮ ያዋጣው ሪፖርት እንደሚያስረዳው የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በቁጥጥር ስር አውለዋቸው የነበሩ አስር ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል።
ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የተሰራጨውን የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች እና በርካታ ተመልካቾች በተሰበሰቡበት አስክሬኖች እና አንድ በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ በእሳት ሲቃጠሉ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በሚመለከት ምርመራ ማድረጉን ገልጿል።
በዕለቱ ግድያው የተፈፀመው ከዳኝነት ውጪ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ አስከሬኖችን አንድ በሕይወት ከነበረ ሰው ጭምር የማቃጠል ድርጊት የተፈፀመው በመንግሥት የፀጥታ አባላት እና በሌሎችም ተሳትፎ ጭምር መሆኑን አመልክቷል።
በምርመራውም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ማንኩሽ እና ባምዛ ይጓዙ በነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ፍተሻ ማካሄዳቸውን ገልጿል።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ፍተሻ ማካሄድ የጀመሩት የካቲት 23/2014 ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች እና ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎቹ ጋር በዕለቱ ሲታኮሱ መቆየታቸውን በነጋታው ተጨማሪ ኃይል ወደ ስፍራው መድረሱን ከዓይን እማኞች መስማቱን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
የፀጥታ አባላቱ ባደረጉት ፍተሻም በቅርቡ ከእስር ተፈትተው ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱና የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩ ስምንት ትግራይ ተወላጆችን በአካባቢው በተፈፀመው ጥቃት መወንጀላቸውን ሪፖርቱ አመልከቷል።
በወቅቱ በተደረገ ፍተሻ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ ከ40ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና የተለያዩ ፎቶግራፎች መያዛቸው ተገልጿል።

ከዚህ በኋላ የመንግሥት ፀጥታ አባላት ተጠርጣሪዎቹን እየደበደቡ ተጨማሪ መረጃ ሲጠይቁ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ "በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ሰዎች አሉን" ማለቱን ተከትሎ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላቱ ሁኔታውን የተቃወሙ ሁለት የጉሙዝ ተወላጆችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል ብሏል።
ከዚህ በኋላም የፀጥታ አባላቱ የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ከከተማው ወጣ ብሎ ወደ ሚገኝ ጫካ በመውሰድ ማቃጠላቸውን ከዓይን ምስክሮች እማኝነት መረዳቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህ መካከል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት አለው የተባለን አንድ ሌላ የትግራይ ተወላጅ በተሳፈረበት መኪና ውስጥ ተደብቆ አግኝተው አስረው በመውሰድ በመቃጠል ላይ ከነበሩት አስከሬኖች ላይ እንደጨመሩት ሪፖርቱ አመልክቷል።
ይህ ተንቃቃሽ ምስል በሰፊው በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከተዘዋወረ በኋላ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን አውግዞ ፈጻሚዎቹን በማጣራት በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ገልፆ ነበር።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከወጣ በኋላም የትግራይ ክልል መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።
ለፀጥታ ኃይሎቹ ድርጊት መነሻው ምን ነበር?
በኢሰማኮ መግለጫ መሰረት ድርጊቱ የተፈፀመው የካቲት 24/2014 ዓ.ም መሆኑን ተመልክቷል።
ይህ ድርጊት ከመፈፀሙ በፊት በክልሉ የካቲት 23/2014 ዓ.ም በመተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ አፍሪካ እርሻ ልማት ማኅበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ማንኩሽ እና ወደ አሶሳ ከተማ እጓዙ በነበሩ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመፈፀም 20 ሰዎችን መግደላቸው ነው።
በጥቃቱም የአንድ መኪና አሽከርካሪ፣ አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰው እና አንድ መምህር በአጠቃላይ 3 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።
መንገደኞቹን አጅቦ በመጓዝ ላይ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኪና በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ሻለቃ አመራሩን ጨምሮ ቢያንስ 20 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተገድለዋል።
14 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።
በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና እና ጥቃቱን በፈጸሙ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተደረገው ውጊያ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ አመሻሽ 12፡00 ሰዓት የቆየ መሆኑን የኢሰመኮ ሪፖርት አመልክቷል።
በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ተጨማሪ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በቦታው ደርሰው ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት ድረስ በቆየ የተኩስ ልውውጥ ከታጣቂዎቹ መካከል ወደ 30 የሚሆኑ መገደላቸውንና ቀሪዎቹ ታጣቂዎች መሸሻቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያስረዳው በወቅቱ በስፍራው የነበሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ነበሩ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ "በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ከዳኝነት ሂደት ውጭ መግደል እና በተለይም በእሳት አቃጥሎ መግደል ፈጽሞ ከሕግ አስከባሪ አባሎች የማይጠበቅ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመሆኑ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ" ጠይቀዋል።















