የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ምን ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, Prosperity
ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት፣ አርብ ማካሄድ ጀምሯል።
ብልጽግና ፓርቲ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ ከትግራይ ክልል ውጪ በተደረጉ ምርጫዎች በአብላጫነት በማሸነፍ አገሪቱን ለአምስት ዓመታት የማስተዳደር መንበሩን ተረክቧል።
ብልጽግና ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ መጋቢት 02/2014 ዓ.ም፣ አርብ ዕለት በደማቅ ዝግጅት የጀመረ ሲሆን፣ ከ1500 በላይ አባላቱ እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ሹም ሽር እንደሚኖር እና ቁልፍ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ ይጠበቃል።
የብልጽግና ምሥረታ
አገሪቱን ለ27 ዓመታት የመራውን ኢህአዴግን በመተካት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመሪነት መንበሩን የጨበጠው ብልጽግና፣ ከቀደምት አባል ፓርቲዎች መካከል ህወሓትን የቀነሰ ቢሆንም በርካታ ክልላዊ ፓርቲዎችን በማካተት ፖለቲካዊ መሠረቱን አስፍቷል።
የአራት ክልላዊ ፓርቲዎች ጥምረት የነበረው ኢህአዴግ፣ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በብቸኝነት ካስተዳደረ በኋላ የገጠመውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ከውስጡ በወጡ መሪዎች አማካኝነት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ራሱን በአዲስ መልክ አዋቀረ።
ኢህአዴግ በአራቱ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ፓርቲዎችን ይዞ በህወሓት አውራነት የተቋቋመና ሲመራ የነበረ ድርጅት ነው።
ይህ የአራት ፓርቲዎች ግንባር በዓመታት ሂደት ውስጥ የገነባው ኃያልነት እየተሸረሸረ ተቃውሞ እየበረታበት እና በውስጡም የተፈጠረው ስንጥቃት እየሰፋ ሄዶ ነበር።
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በጋራ የሕዝቡን የለውጥ ጥያቄ ለመመለስ እርምጃ መውሰድ ቢጀምሩም፣ የግንባሩ አውራ የነበረው ህወሓት፣ ከአጋሮቹ ጋር የነበረው ትስስር እየላላ በሄደበት ጊዜ ቀሪዎቹ ፓርቲዎች ውህድ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ልዩነታቸው ጎልቶ ወጣ።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉት የሚነገረውን ኢህአዴግን፣ ውህድ አንድ ወጥ ፓርቲ የማድረግ ሐሳብ በግንባሩ የተነሳው ከዓመታት በፊት ቢሆንም ከለውጡ በኋላ በእጅጉ ተጠናክሮ ወደ ተግባር የተሻጋገረው ግን ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ኢህአዴግ ፈታኝ የነበረውን የአመራር ለውጥ ካደረገ በኋላ ሐዋሳ ላይ ባደረገው 11ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ አንድ ወጥ ፓርቲ የመሆን ውሳኔን አሳልፏል።
በወቅቱ ይህ ሂደት መዘግየቱ ተጠቅሶ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን የግንባሩ አባል ፓርቲዎች በጋራ ወስነው ነበር።
ነገር ግን ይህ ውህድ ፓርቲ የመመስረት ሂደት በግንባሩ ውስጥ ሙሉ ድጋፍን አላገኘም።
ሂደቱ በህወሓት በኩል ጥያቄዎች ተነስተውበት ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢካሄዱም፣ ብልጽግና ህወሓትን ይዞ ለመቀጠል ሳይችል ቀርቷል።
በመጨረሻም ከህወሓት ውጪ ያሉት የግንባሩ አባላት ውህደቱን ተቀብለው አዲሱ ፓርቲ ይፋ ሆነ።
ብልጽግና ህወሓትን ሳያካትት ቢመሰረትም ቀደም ሲል ኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚላቸውን በማካተት ሰፊ መሰረት ያለው አገራዊ ፓርቲ ለመሆን ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉትም ፓርቲው ከ11 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ግዙፍ የፖለቲካ ድርጀት ለመሆንም በቅቷል።
የብልጽግና ፈተናዎች
ብልጽግና አንድ ወጥ ፓርቲ ሲሆን ቀደም ሲል በኢህአዴግ ውስጥና በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ግዙፍ ተጽእኖና የበላይነት የነበረው ህወሓት መነጠሉ ጥርጣሬና ስጋትን ማስከተሉ አልቀረም።
በወቅቱም በህወሓትና በብልጽግና መካከል አልፎ አልፎ መወቃቀስ መታየት ጀምሮ ቀስ በቀስ ወደ መወነጃጀል አድጎ ነበር።
በዚህም ሳያበቃ በኢህአዴግ ዘመን ከህወሓት ወገን በፌደራልና በአዲስ አበባ በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ላይ ተመድበው የነበሩ አባላት ፓርቲው ከብልጽግና ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ የበለጠ መካረርን ፈጠረ።
የህወሓት ራሱን ከብልጽግና ማራቁ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሁለቱም በኩል የነበረው መወቃቀስ እየገፋ ሄዶ የትግራይ ክልል እና የፌደራል መንግሥቱ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ሳይሆን ሁለት አቻ መስተዳደሮች እስከ መምሰል ደርሰው ነበር።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ይህንን ተከትሎም ስድስተኛውአገራዊው ምርጫ መራዘም ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው ቅሬታን ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል።
በተለይ በትግራይ ውስጥ በተናጠል የተደረገው ምርጫ በህወሓት እና በብልጽግና እንዲሁም ሁለቱ ፓርቲዎች በሚመሯቸው በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረውን መቃቃር ወደማይታረቅበት ደረጃ አደረሰው።
በትግራይ ከተደረገው ምርጫ በኋላ ሁለት ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የተቀሰቀሰውና እስካሁንም መቋጫ ያላገኘው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ይህንንም ተከትሎ 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የአገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በበላይነት ሲመራ የነበረው ህወሓት በሽብርተኛ ቡድንነት ተፈረጀ።

የፎቶው ባለመብት, Prosperity
ጦርነት እና የኑሮ ውድነት
የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤውን በደማቅ ሁኔታ ማካሄድ የጀመረው ብልጽግና ከተመሰረተ በኋላ በነበሩት ባለፉት ዓመታት ከባድ ፈተናዎች ገጥመውታል። በተለይ በትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው እና ለ16 ወራት ያህል የዘለቀው ጦርነት መሪውን ጭምር ወደ ጦር ግንባር እንዲሄዱ ያደረገ አገራዊ ፈተና ነበር።
ጦርነቱ በአንድ ክልል ብቻ የተገደበ ሳይሆን የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ያዳረሰ አገሪቱንም ከባድ ፈተና ውስጥ የከተተ ነው። ይህ ጦርነት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያንና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ከማመሳቀሉ ባሻገር ጫናና እቀባዎችን አስከትሎባታል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥም የሚንቀሳቀሰው እና በአሸባሪነት የተፈረጀው፣ የኦነግ ሸኔ ሸማቂ ቡድንም የሚያደርሰው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ በመሄድ ሌላኛው የመንግሥት ራስ ምታት ከሆኑ ቆየት ብሏል። በዚህ ሳቢያ ሰላማዊና የተረጋጉ የነበሩ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሞትና መፈናቀል በተደጋጋሚ የሚሰማባቸው ሆነዋል።
በአማራ እና በአፋር ክልል ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ የደረሰው ውድመትና መፈናቀል ብልጽግና ከሚመራው መንግሥት መፍትሄ ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል አንገብጋቢው ነው።
ከጦርነቱ ባሻገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነት ሁኔታ በከተሞችና በገጠር ያለውን ሕዝብ በየዕለቱ የሚያስጨንቀው ዋነኛ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች የተካሄደው ጦርነት ካስከተለው መጠነ ሰፊ መፈናቀል በተጨማሪ ለተከታታይ የግብርና ወቅት የእርሻ ሥራ በማደናቀፉ ይገኝ የነበረን ምርት ማስቀረቱ በርካቶችን የእርዳታ ጠባቂ ያደርገዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአብዛኛው የደቡብና ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ለተከታታይ ጊዜ ሳይገኝ የቀረው ዝናብና የአንበጣ ወረራ ድርቅና ረሃብን እያስከተለ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው።
አስካሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንሰሳት መሞታቸው የተነገረ ሲሆን በቀጣይ ወራት ሕዝቡ ለከፋ ረሀብና ሞት ሊደረግ እንደሚችል ከፍ ያለ ስጋት አለ።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያጋጠሙት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች፣ ምጣኔ ሀብታዊ ፈተናዎች እንዲሁም የሰላም መደፍረስ በተለይም ከህወሓት ጋር የሚደረገው ጦርነት የሚቋጭበት መንገድ ብልጽግናን እንደ ገዢ ፓርቲ የሚፈትኑት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።
ጠቅላላ ጉባኤው
በበርካታ ታዛቢዎች ከዚህ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ከተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ የተሻለ ተዓማኒነት እንዳለው የተነገረለትና ባለፈው ዓመት በተደረገው ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በበላይነት ያሸነፈው ብልጽግና የኑሮ ውድነት ጫናን እንዲያረግብና ሰላምን እንዲያመጣ መራጩ ይጠብቀዋል።
በተለይ ባለፉት ወራት የታዩት የጦርነቱ መስፋፋት እና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ሕዝቡ እንዲያስተዳድረው ወደ መረጠው ፓርቲ ለመፍትሄ እንዲያማትር አድርጎታል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የሚካሄደው የመጀመሪያው የብልጽግና ጉባኤ ደግሞ ከዚህ አንጻር ቁልፍ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎታል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት ቀናት በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰጡት ፍንጭ መሰረትም ፓርቲውን በየደረጃው ከማጠናከር ባሻገር የተለያዩ ተግባራት እንደሚያከናወኑና ከፓርቲው አላማ ጋር አብረው መራመድ ካልቻሉ ግለሰቦች የማጥራት እርምጃ እንደሚወሰድ በአለፍ ገደም አመልክተዋል።
የብልጽግና የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳም የፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ "የሕዝብ አደራን በብቃት የሚወጡ ጠንካራ አመራሮች የሚመረጡበት" እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ በተለይ በአንጋፋዎቹ የፓርቲው አባል ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመንቀስ ፓርቲው ከገጠሙት ፈተናዎች እንዲሁም ሕዝቡ ከሚጠብቀው ውጤት አንጻር በአመራሩ ላይ ለውጦች እንደሚኖሩ በስፋት እየተነገረ ነው።
እንዲሁም ፓርቲው አገሪቱ ከገጠማት ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ በተለይም እየተካሄደ ካለው ጦርነት አንጻርም ቁልፍ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ እንዳሉትም ይህ የብልጽግና ጠቅላላ ጉባኤ ጠንካራ አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ የሚደረግበት እና ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ይሆናል።
ይህም መጋቢት አርብ 02/2014 ዓ.ም በደማቅ ዝግጅት የተጀመረውና ቅዳሜና እሁድ በሚቀጥለው ከ1500 በላይ አባላቱ በሚሳተፉበት የመጀመሪያው ጉባኤ ማብቂያ ላይ ይፋ የሚሆን ነው።















