የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት እጥረት አዙሪት እና ምክንያቱ

የፎቶው ባለመብት, Matthew Horwood
ከሰሞኑ የምግብ ዘይት ዋጋ መናር የኢትዮጵያውያን ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።
ትልቁን የገበያ ድርሻ በሚይዘው የፓልም ዘይትም ሆነ በሱፍ (ሰንፍላወር) ዘይት ላይ ድንገተኛ የሆነ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ይህም በተጠቃሚው ላይ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል።
በ6500 ወርሃዊ ደሞዝ 7 የቤተሰብ አባላት የሚያስተዳድሩት አንድ የመንግሥት ሠራተኛ፤ 5 ሊትር የፓልም ዘይት ከ1000 አስከ 1200 ብር እየገዙ መሆኑን በመናገር፤ " . . . አንድ ፍሬ ሳሙና ከ26-30 ብር እየተገዛ፤ ለተለያዩ ጉዳዮች ከደሞዝ እየተቆረጠ መኖር በጣም ከባድ ነዉ" በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
አቶ ነጌሳ ቱካና ደግሞ በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ የአንድ አነስተኛ ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው። በቀን ከ80 እስከ 100 ለሚሆኑ ተጠቃሚዎችም ምግብ ይሸጣሉ።
"ሦስት ሊትር ዘይት 550 ብር ገብቷል። እሱ ራሱ አይገኝም። ለምግብ ቤቶች ሥራ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል" ይላሉ።
በዘይት የችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት የመንዲ ከተማ ነጋዴው በምርት እጥረት እና ዋጋ ንረት የንግድ ሥራቸው መቀዛቀዙን ይናገራሉ።
የዘይት ዋጋ በኢትዮጵያ በድንገት ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
እንደው በድንገት የዘይት ዋጋ ለምን ጣራ ይነካል? ስንል አምራቾችን፣ ጅምላ አካፋፋዮችን፣ ቸርቻሪዎችን እና የሚመለከተውን የመንግሥት አካል ጠይቀናል።
የኢትዮጵያ የዘይት ምርት እና ፍጆታ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ፉድ፣ ቤቨሬጅ ኤንድ ፋርማሱቲካል ዲቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢትዮጵያ እና ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢምፕሩቭድ ኒዩትሪሸን የሰሩት ጥናት በአገሪቱ የዘይት ገበያ ላይ የፓልም፣ የሱፍ፣ የአትክልት፣ የወይራ (ኦሊቭ ኦይል) እና የሶያ ዘይት አይነቶች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አሳይቷል።
ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ ኢትዮጵያ እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን የዘይት ፍላጎቷን በፓልም ዘይት የምታሟላበት ዓመታት አሉ።
ኢትዮጵያ በፓልም ዘይት ምርታቸው ከሚታወቁት ኢንዶኔዢያ እና ማሌዢያ ከፍተኛ መጠን ያለው የፓልም ዘይት ታስገባለች።
ታዲያ የፓልም ዘይትን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸው የነበሩት መንግሥታዊዎቹ አለ በጅምላ እና ጅንአድ ናቸው።
በእነዚህ የመንግሥት ተቋማት በኩል የሚገባው ፓልም ዘይት ለተጠቃሚዎች የሚደርሰው በሸማቾች ማኅበራት በኩል ነው።
እንደ ፌቤላ እና ሸሙ ያሉት የግል የዘይት ፋብሪካዎችም የፓልም ደፍድፍ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በአገር ውስጥ የፓልም ዘይት ያመርታሉ።
የተቀሩትን የዘይት አይነቶች ደግሞ የግል ተቋማት በኢትዮጵያ እንዲያመርቱ እና ከውጪ እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸዋል።
የሰሞኑ የዘይት ዋጋ ጭማሪ
በቅርቡ ላገጠመው የዘይት ዋጋ ጭማሪ፤ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እስከ 'የተጋነነ ትርፍ ፈላጊ ነጋዴዎች' በምክንያትነት ቀርበዋል።
ዘይት አምራቾች ምን ይላሉ?
የዛሬ አንድ ዓመት ፌቤላ የተባለው ግዙፉ የዘይት ፋብሪካ ተመርቆ ወደ ሥራ ሲገባ፤ የኢትዮጵያን የዘይት እጥረት ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቡሬ ከተማ ተገኝተው ፋብሪካውን መርቀው ከፍተዋል። በወቅቱም 60 በመቶ የኢትዮጵያን የዘይት ፍላጎትን ያሟላልም ተብሎለት ነበር - ፌቤላ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ።
ነገር ግን ዛሬም የዘይት ዋጋ መናር ብዙዎችን እንዳማረረ ቀጥሏል። ፋብሪካው በበኩሉ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ብዙ ፈተኛ ሁኔታዎች ቢገጥሙኝም የተቻለኝን ሁሉ እያደረኩ ነው ይላል።
ፌቤላ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ አካል ሲሆን የኩባንያው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳው፣ ፋብሪካው ባለፈው አንድ ዓመት 166 ሚሊዮን ሊትር የፓልም ዘይት አምርቶ ማከፋፈሉን ይናገራሉ።
አቶ ሰጠኝ ፋብሪካቸው በአምስት ዙሮች 105 ሺህ ሜትሪክ ቶን የፓልም ድፍድፍ ዘይት ከውጪ ማስመጣቱንም አመልክተዋል።
በሊትር ከ40 ወደ 82 ብር
ከአንድ ዓመት በፊት ፋብሪካው 1 ሊትር ዘይት በ40 ብር ለገበያ ሲያቀርብ እንደነበረ የሚያስታውሱት አቶ ሰጠኝ፤ ዛሬ ላይ ግን የ1 ሊትር የፓልም ዘይት ዋጋ 82 ብር መሆኑን ይናገራሉ።
ፋብሪካው ዋጋውን በእጥፍ እንዲጨምር ያስገደዱት በርካታ ምክንያቶች ናቸው በማለት፣ የመጀመሪያው የፓልም ድፍድፍ ዘይት ዋጋ መጨመርን ይጠቅሳሉ።
"አንድ ሜትሪክ ቶን የፓልም ድፍድፍ ዘይት 762 ዶላር ነበር የምንገዛው። 4ኛው ዙር ላይ ለአንድ ሜትሪ ቶን 1361 ዶላር ከፍለናል። አሁን እያሰራጨን ያለነው ዘይት ደግሞ በ5ኛው ዙር በ1407 ዶላር ተገዝቶ በገባ ድፍድፍ ፓልም የተመረተ ነው" በማለት የዋጋውን ጭማሪውን ያስረዳሉ።
ከፓልም ድፍድፍ ዘይት መወደድ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የደኅንነት ስጋት፣ የአገር ውስጥ ግብዓት ዋጋ ጭማሪ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሌሎች ለፋብሪካው ፈተኛ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ናቸው ይላሉ።
አቶ ሰጠኝ ፌቤላ ባሉት ግዙፍ 5 ማሽኖች አማካይነት በቀን እስከ 1.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ቢኖረውም አሁን ላይ የምርት አቅማቸው በግማሽ መገደቡን ይጠቅሳሉ።
"በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በቀን 750 ሺህ ሊትር ብቻ ነው የምናመርተው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ የነዳጅ መጠን የሚጠቀሙ ጀነሬተሮችን ገዝተን እየተጠቀምን ነው።"
በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ከቅባት እህሎች ዘይት ለማምረት የሚያስፈልገውን ግብዓት ማቅረብ የሚችል የአገር ውስጥ አቅራቢ ባለመኖሩ፣ ለዘይት ምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማግኘት የራሱ እርሻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ አለው።
ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር የእርሻ ሥራቸው ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገው አቶ ሰጠኝ ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፌቤላ ፋብሪካ አንድ ሊትር በ82 ብር ለአካፋፋዮች ያቅርብ እንጂ ቢቢሲ ባደረገው ቅኝት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ባለ 1 ሊትር ፓልም ዘይት እስከ 150 ብር፣ ባለ 3 ሊትር 550 ብር እና ባለ5 ሊትር ደግሞ በትንሹ 900 ብር ይጠየቅበታል።
ለባለ 1 ሊትሩ ሰንፍላወር ዘይት ደግሞ ከ180 አስከ 190 ብር ይጠየቃል።
አቶ ሰጠኝ ግን "አከፋፋዮች አሁን (ማክሰኞ የካቲት 29) ፋብሪካ በር ላይ 1 ሊትር ፓልም ዘይት በ82 ብር ነው እየጫኑ ያሉት" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, FBC
ይህ ሰፊ የዋጋ ልዩነት ከየት መጣ?
"ጭማሪው እኛን አይመለከትም" ይላሉ አቶ ሰጠኝ፤ ፋብሪካው ከመንግሥት በተሰጠው ኮታ መሠረት ለ7 ክልሎች እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከላይ በተጠቀሰው የፋብሪካ ዋጋ የፓልም ዘይት እያከፋፈለ እንደሆነ በመጥቀስ።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈገ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው የሽያጭ ባለሙያ፤ ከፍተኛ ፍላጎት ባለባቸው የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ የሚተመነው በግለሰቦች ፍላጎት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ ዘይትን ጨምሮ መሠረታዊ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እና በማከፋፈል ሂደት ውስጥ የበርካታ ዓመታት ልምድ ያለው የሽያጭ ባለሙያ እንደሚለው፤ በመሠረታዊ ሸቀጦች አስመጪዎች ከ30 በመቶ ያላነሰ ትርፍ መያዛቸው የተለመደ ነው።
የሽያጭ ባለሙያው እንደሚለው ከሆነ የዘይትም ሆነ የሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች የሽያጭ ዋጋ የሚተመነው ምክንያታዊ በሆኑ ምጣኔ ሃብታዊ ስሌት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በግለሰቦች ፍላጎት ነው።
አስመጪዎች ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ከባንኮች ማግኘት ስለማይችሉ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ይገደዳሉ።
እናም በተለያየ መንገድ ያገኙትም የውጭ ምንዛሪ የሚያካክሱት በሚያስገቡት ምርት ላይ ዋጋ ያስፈልገናል የሚሉትን በመጨመር ነው ይላል የሽያጭ ባለሙያው።
'የውጭ ምንዛሬ ታጣ ይሉናል'
ዘይት ከአስመጪዎች በመግዛት በጅምላ እና በችርቻሮ ለተጠቃሚዎች የሚያደርሱት የመንዲ ከተማ ነጋዴ በአካባቢያቸው የምርት እጥረት መኖሩን ይናገራሉ።
"ዘይት ከእዲስ አበባና ከአዳማ ነበር የምናመጣዉ። አሁን ግን አጥተናል፤ ማምጣት ልቻልንም" ይላሉ።
"አስመጪዎችን ስንጠይቅ 'የውጭ ምንዛሬ ታጣ' ይሉናል" በማለት የሚሰጣቸውን ምላሽ ይናገራሉ።
የንግድ ሰንሰለት ርዝመት
የሽያጭ ባለሙያ ዘይትን ጨምሮ በሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት የሚያደርገው ሌላኛው ትልቁ ምክንያት የንግድ ሰንሰለቱ መርዘም ነው ይላል።
"የንግድ ሰንሰለቱ በጣም ረዥም ነው። አስመጪዎች ምርቱን ከሞጆ ደረቅ ወደብ አንስተው መርካቶ ያስገባሉ። አስመጪዎች ዋጋ ተምነው ለጅምላ አካፋፋዮች ያደርሳሉ" በማለት የገበያ ሰንሰለቱን ሂደት ያብራራል።
"ከዚያም ጅምላ አፋፋዮች ደግሞ የራሳቸውን ትርፍ ይዘው ክፍለ አገር ላለ ሌላ ጀምላ አከፋፋይ ያደርሳሉ። እነዚህ ጀምላ አካፋፋዮች ደግሞ ለቸርቻሪ ይሸጣሉ። ቸርቻሪ በነጠላ እቃ ላይ ብዙ ትርፍ ይይዛል። በመጨረሻ ዘይቱ ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ ዋጋው ይከመራል።"
ከዚህ በተጨማሪም አቅም ያለው ተጠቃሚ ደግሞ "ገና ለገና 'ዘይት ጠፋ ሲባል' ከሚያስፈልገው በላይ ካርቶን ሙሉ ገዝቶ ስለሚያስቀምጥም ፍላጎት እንዲጨመር ያደርጋል" በማለት ተጨማሪ ምክንያት ያስቀምጣል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት
በንግድ እና የቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አበባ ታመነ ከሰሞኑ ለተከሰተው የዘይት ዋጋ ጭማሪ ዋነኛ ምክንያቱ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ነው ይላሉ።
ወ/ሮ አበባ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ከተማ ያጋጠመው የሰንፍላወር (የሱፍ) ዘይት እጥረት እንጂ የፓልም ዘይት አይደለም።
ዩክሬን ከፍተኛ የሱፍ ዘይት አምራች አገር መሆኗን በማስታወስ፤ በጦርነቱ ምክንያት አስመጪዎች ምርት ማግኘት ባለመቻላቸው እጥረት አጋጥሟል ይላሉ።
"በራሳቸው ዶላር ምርት ያገኙት እንኳ 'ዋጋ እየጨመረ ስለሚሄድ ነገ እና ከነገ ወዲያ የተሻለ ትርፍ አገኛለሁ' በሚል አስተሳሳብ ጂቡቲ ወደብ ላይ ምርት የሚያቆዩ ነጋዴዎች ስላሉ እጥረቱ ሊያጋጥም ችሏል" ይላሉ።
የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ሰኞ የካቲት 28/2014 ዓ.ም ለቢቢሲ በተናገሩበት ቀን፤ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከሳዑዲ አረቢያ ለማስገባት ስምምነት መጨረሱን ተናግረው ነበር።
"በአካል ተገናኝተው ከስምምነት ተደርሷል። 20 ሚሊዮን ሊትሩ የሰን ፍላወር ነው ቀሪው ፓልም ነው። ይህ ዘይት በቅርብ ቀን ይገባል ገበያውንም ያረጋጋል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ወ/ሮ አበባ ይህን ይበሉ እንጂ የገንዘብ ሚኒስቴር 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለመግዛት ከስምምነት አለመድረሱን እና ጉዳዩ ገና በጥናት ላይ እንደሚገኝ ስለመናገሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
















