"በቁመት ከኢትዮጵያ አንደኛ ነኝ"-ብርሄ ጋሹ

ብርሄ ጋሹ

የፎቶው ባለመብት, Awi communication

ቢቢሲ በቅርቡ ነጋዎ ጂማ የሚባል ወጣትን እንግዳው አድርጎ ነበር።

ዛሬ ደግሞ ብርሄ ጋሹ ስለሚባል ሰው እንጨዋወታለን።

ነጋዎ ዕድሜው 24 ነው። ብርሄ ደግሞ 38 ደርሷል።

ነጋዎ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የመቂ ከተማ ነዋሪ ነው።

ብርሄ ደግሞ ነዋሪነቱ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ ድማማ አንገረፍ ቀበሌ ነው።

ነጋዎ የሚጫማው 54 ቁጥር ሲሆን ብርሄ ግን በህይወቱ ጫማ ተጫምቶ አያውቅም።

የ24 ዓመቱ ወጣት ቁመቱ 2.25 ሜትር የደረሰ ሲሆን የንገረፍ ቀበሌው ነዋሪ ደግሞ 2.50 ሜትር ደርሷል።

ታዲያ ሁለቱን ኢትዮጵያዊያን ምን አመሳሰላቸው? ቁመት።

ስለ ነጋዎ ህይወት ቀጥሎ ካለው ሊንክ ያንብቡ።

አሁን ብርሄ ላይ ትኩረት እናድርግ።

ብርሄ አንቱ እያለን ላቀረብንለት ጥያቄ "አንተ ነው መባል ያለብኝ አንቱማ መነኩሴ ስሆን ነው" ሲል ጨዋታውን ጀመረ።

ነዋሪነቱ አዊ ብሔረሰብ ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ ድማማ አንገረፍ ቀበሌ ነው። አንገረፍ ጊዮርጊስ በምትባል ልዩ ጎጥ።

ህጻን እያለ ከጓደኞቹ የተለየ አልነበረም።

ብርሄ ቁመቱ የተመዘዘ መሆኑን ያወቀው ስድስት ዓመት ከሆነው በኋላ ነው።

ከዚያማ ማን በስሙ ይጥራው። ብርሄ ተረስቶ ዛፉ፣ ዝግባው. . . ሆነ መጠሪያው።

እሱም ቢሆን ራሱን ሲያስበው ከገበያውም ከአካባቢው ሰውም ልዩ መሆኑ ይሰማው ጀመር።

"ሰው በታች እያለ እኔ በፈረስ ላይ ሆኜ እንደምሄድ ነው የምታየው" ሲል ይገልጻል።

እየዋለ እያደረ ደግሞ ችግር መጣ።

ሥራ መስራት አልቻለም።

ማረስ ፈተና ሆነ። ለበሬዎቹ የሚስማማው ሞፈር እና ቀንበር ብርሄን አስጎንብሰው ወገቡን ሊሰብሩት ደረሱ።

ለምን በቁመቴ የሚስማማ አላደርግም ሲል ደግሞ በሬዎቹ አልተመቻቸውም ለገሙ። አልንቀሳቀስ አሉ።

ፈተናው ይህ ብቻ አይደለም። የሚበቃው ልብስ ስለማያገኝ ሲያሰፋ "ካለው ህብረተሰብ በላይ ነው" ጨርቁ የሚያስወጣው።

"ልብስማ ያው ወጪ ይጠይቀኛል እንጂ ሁለት ሰው የሚለብሰውን ባለሙያዎች ይሰሩልኛል። ልብስ ሳሰፋ እንደ ጨርቁ ሁኔታ ለሁለቱ ሰው የሚሆነው ለእኔ ይበቃኛል። ለአንድ ጊዜ 1500 ብር እንደዛ እከፍላለሁ። የሁለት ሰው ሂሳብ ነው የምከፍለው" ሲል ያስረዳል።

እግሩም ጫማ አይቶ አያውቅም። የጫማ ቁጥሩንም አያውቀውም።

"ጫማ የማልለብስብት ምክንያት እግሬም እንደቁመቴ አብሮ ስላደገ የተሠራው ጫማ የማይበቃኝ ነው" ይላል።

"ጫማ ቁጥሩን አላውቅም አድርጌም አላውቅም። ጫማ የሚባል ከእግሬ ገብቶ አያውቅም። ከተወለድኩኝ ጫማ አድርጌ አላውቅም። እኔ እግሬ ትልቅ ስለሆነ ነው። ሁሌም ስለማላደርግ እግሬ ተሰነጣጥቋል"

ቁመቱ 2.50 ሜትር ደርሷል፤ በተደጋጋሚ ተለክቶ አረጋግጧል።

ቤተሰቦቹ 'ቁመትህ እንደ ጓደኞችህ ቢሆን ዓይን ውስጥ አትገባም ነበር" እንደሚሉት ደጋግሞ ይገልጻል።

ካልሆነም ተወዳድሮ 'ልዩ ነገር' ማግኘት እንደነበረበት ሁሌም ያነሳሉ።

ለዚህም ነው 'ከሁለት አንድ ያጣህ ጎመን ሆንክ ይሉኛል' የሚለው።

ብርሄ የፊደል ዘር አልቆጠረም።

ምከንያት ሲባል "ወላጆቼ ምስኪን ነበሩ" ሲል ይመልሳል።

ከዘጠኝ ዓመቱ ጀምሮ ሰው ቤት ነው ያደገው። "ህጻን ስለሆንኩኝ እናት አባቴን አገለግላለሁ በሚል እንጂ እንደዚህ እጉላላሁ ብዬ አላሰብኩም አሁን ግን አዝናለሁ ብማር ኖሮ ራሴም አልጉላላለም ቤተሰቦቼንም እረዳ ነበር እላለሁ።"

ብርሄ ጋሹ

የፎቶው ባለመብት, Awi communication

ቢቢሲ፡ ቁመቴ ረዥም ባልሆነ ብለህ ታውቃለህ?

ብርሄ፡ አዎ

ቢቢሲ፡ መቼ?

ብርሄ፡ ሁለት ጊዜ ወድቄ በተሰበርኩ ጊዜ፣ ቁመቴ ረዥም ባልሆን ብወድቅም እንኳን እነሳ ነበር። ብዙዎች አጠገቤ እየወደቁ ሳይሰበሩ ምንም ሳይሆኑ ይነሳሉ አያቸዋለሁ። እኔ ግን ስወድቅ ሁለቱም ጊዜ አንዴ ቀኝ እጄን ሌላ ጊዜ ደግሞ ግራ ጫንቃዬን ተሰበርኩ። ዘንድሮ መስከረም ላይ፤ በዚህ በዚህ ቁመቴን አማርራለሁ። ሁለተኛ መሥራት ስችል ያለው ህብረተሰብ እንዳሻው ሲያርስ እና ሲያጭድ ሳየው እና እኔ እንደዛ መሆን ሲያቅተኝ ስሜታዊ እሆንና እናደዳለሁ።

ቢቢሲ፡ እንኳንም ረዥም ሆንኩኝ ያልክበት ጊዜ አለ?

ብርሄ፡ አንዳንዴ ከላይ ያሉትን ነገሮች ሳወርድ፤ ሌላው የማያወርደውን ሳወርድ ደስ ይላል። ከታች ያለውን ለማንሳት ነው እንጂ ፤ከላይ ያለውን ለማውረድ ለእኔ የላይኛው ስለሚቀርበኝ ለእኔ ደስ ይላል። አሁን ደግሞ አሁን ደግሞ ቀረጻ እና ቃለ መጠይቅ ሲደረግልኝ ተስፋ አለው መስል ከሌላው ህብረተሰብ ቁመቴ ስላደገ አይደል እላለሁ።

ብርሄ ማረስ፣ ማጨድ እና ማረም አይችልም።

"የሚያሰቸግረኝ በጣም ዝቅ ስል ወገቤ እና አንገቴ ይወጣ እና ስሜታዊ ያደረግኛል" ይላል።

እንዲህም ቢሆን የሚተዳደረው በእርሻ ነው።

ምስጋና ለባለቤቱ። ባለቤቱ ሁሉንም ትሠራለች።

ጎረቤትም በእርሻ ሥራ ከጎኑ አልተለየም።

"ማህበረሰቡ በሙሉ እንደዚህ ሆንክ በሚል ለእኔ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልህ እያለ የሚቆረቆር ነው። በአጫዳም ሆነ በእርሻ ያግዘኛል። በልማት እና በጥበቃም አያዘኝም። የኔን ኮታ ህብረተሱቡ ነው የሚሸፍነው።"

መኖሪያ ቤቱ እንደ ኅብረተሰቡ ነው የተሠራው። በሩም ተመሳሳይ ነው። ሲገባ እና ሲወጣ እያጎነበሰ ነው።

አልጋ ከሌሎች ረዘም ተደርጎ ተሰርቶለታል።

"ሌላ አልጋ ላይ ስተኛ በአንድ በኩል በጣም ይተርፋል። በዛ ጉዳይ ላይ ደግሞ ወገል እና ማረሻ ከተገጣጠመ ችግር የለውም [ሳቅ]።"

ብርሄ ባለትዳር ነው። የመጀመሪያ ልጁን የወለደችለት ሚስቱ አልፈልግም ብላ ትላው ሄደች።

በኋላም በተደጋጋሚ አጨ። እነሱም አንፈልግም አሉ።

አሁን ካገባት ሚስቱ ጋር ሦስት ልጆች አፍርተዋል።

የአንድ ሴት እና የአራት ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል።

"እምቢ የሚሉት ረዥም ነው ሰርቶ አያበላንም። አንዳንዱ ደግሞ ይኼን ሰውዬ አያችሁት እያለ ስለሚስቅ ስለሚሳቅባቸው ነውር ይመስላቸዋል ለዛም ነው" ይላል።

"አሁን ያለችው ሚስቴ በአጨዳው በምኑ ሥራ ሲበዛባት አንዳንዴ እንዲህ ሆነህ [ቁመትህ ረዝሞ] ተቸግረህ እኔም ተቸግሬ ብላ ይሰማታል እንጂ ከዛ ውጭ ፍቅረኛ ነን።"

እንደሱ ረዥም ቁመት ያለው በቤተሰቡ የለም።

ብርሄ ጋሹ

የፎቶው ባለመብት, Awi communication

ብርሄ "ቆሜ ሌሎች የማያያዩትን ነገር አያለሁ። ፈቀቅ ያለ ከማዶ ወደ ተራራ አካባቢ ሌሎች የማያዩትን እኔ ማየት እችላለሁ" እያለ ያስረዳል።

ሴት ልጁ ግን ረዥም እንደምትሆን ይገምታል። "የመጀመሪያ ሴት ልጄ አገዳዋን ሳየው እንደኔ ባትሆንም ረዥም ነው። 10 ዓመቷ ነው፤ ሳየው አገዳዋ፣ ጣቷ፣ አንጓዋንና እጇን ሁኔታዋን ሳየው ረዥም ትመስለኛለች። ሌላው ወገኔን ሳየው አጭር ነው እንደኔ ቀርቶ የኔን ግማሽ አይሆንም" ብሏል።

"ልጆቼ ጨቅላ ናቸው፤ ጨቅላ ስለሆኑ ገና ትንሽ ስለሆኑ [ረዥም ልሁን አጭር] ብዙም ገንዘብ ብለው አያውቁም። ያው ብቻ በጣም ይወዱኛል። ለትንሽ ደቂቃ ተለይቻቸው ስመጣ ብርቀኛ ሆነው መጣ መጣ እያሉ ይደሰታሉ።"

በዚህ ቁመቱ ምክንያት ምን ገጥሞት ይሆን?

"አንዲቱ ገበያ እያለሁ ከታች እግሬን ቆነጠጠችኝ። ዞር ብዬ ሳያት 'ለካ ይሄ ሰውዬ ይሰማል' ብላኛለች። [ሳቅ] በዚህ በዚህ ይሰማኛል።"

"ጸባዩ ጥሩ ነው። በዚህ ቁመቱ ክፉ ቢሆን ሰው ይረብሽ ነበርም " ይላል።

አንዴ ደግሞ ሥራ ፍለጋ ብሎ ወደ ሸገር አቀና።

ያረፈበትን ቤት ሰዉ ከበበው። ሊያየው ከየአቅጣጫው ሰው ተሰበሰበ።

በኋላ ስልክ ፖሊስ ጋር ተደውሎ በፖሊስ ሰዉ መበተኑን ያስታውሳል።

ሥራ አግኘቶ ቢጀመርም ከቀናት በዘለለ አልሠራም።

ተመልሶ ወደ አንገረፍ አቀና።

ሌላው ከባድ ችግር ትራንስፖርት ነው።

መኪና ላይ ወንበሩ እግሬን ስለማይመቸኝ ዳር ላይ ሆኜ እንጂ እንዳሻኝ አልሆንም። ሾፌሮች እና ረዳቶች የሁለት [ሰው] ቦታ ስለምትይዝ የሁለት ሰው መክፈል ነበረብህ ይሉኛል።"

"ሁለት ሰው ይዘን ነበር የምንሄደው እያሉ ገበያም ስንሄድ ሞተረኞች የሁለት ሰው ይቀበሉኛል" ይላል።

በቅርቡ በአካባቢው ያለው የልማት ሥራ ለመጎብኘት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ወደ አንገረፍ አቅንተው ነበር።

ብዙ እንግዶችም አብረዋቸው ነበሩ።

ብርሄም ተጠርቶ ርዕሰ መስተዳደሩን አግኝቷል።

አብረውም ፎቶ ተነስተዋል።

ዕድሜው 38 በመድረሱ ከዚህ በኋላ ቁመቱ የሚጨምር አይመስለውም።

ወደፊትም በቁመቱ መወዳደር ይፈልጋል።

"የወደፊት ዕቅዴ ተወዳድሮ ማሸነፍ ነው። ተወዳድሬ ከኢትዮጵያ አንደኛ መውጣት አለብኝ። አሁንም አንደኛ ነኝ። ተወዳድሬ ማሸነፍ አለብኝ ነው እቅዴ።"

በዚህም መታወቅ ይፈልጋል።

አሸንፎ "ሙሉ ጨርቅ ልብስ እና ጫማ" እንዲኖረው ያስባል። ልጆቹን እንዳሻው ሠርቶ ስለማያኖራቸው "ቋሚ ደሞዝተኛ በመሆን" ልጆቹንም በትክክል መምራት ያፈልጋል።

ቢቢሲ፡ ከሰው ተለየ ምግብ ትመገባለህ?

ብርሄ፡ ከሰው የተለየ ምግብ አልበላም። ከህብረተሰቡ የተወሰነ ጭማሪ ብበላ ነው። ጭማሪውም ተወሰነ ነው ግን የምጨምረው።