2.25 ሜትር የሚረዝመው የመቂ ከተማ ወጣት፤ ቁመቴ ሕይወቴን አክብዶታል አለ

የፎቶው ባለመብት, FIB TV
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የመቂ ከተማ ነዋሪ የሆነው ነጋዎ ጂማ ረዥሙ ቁመቴ ማኅበራዊ ሕይወቴን ከባድ አድርጎታል አለ።
የ24 ዓመቱ ወጣት፤ የሚሆነውን ጫማ እና አልባሳት ማግኘት እንዲሁም የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም እንደ ከበደው ይናገራል።
ነጋዎ የሚጫማው 54 ቁጥር ነው። በሰውነቱ ግዝፈት ምክንያት፤ ልብስ ለማሰፋትም ሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጠቀም ሁለት እጥፍ እንዲከፍል ይጠየቃል።
ነጋዎ "ራሴን መቻል ያለብኝ እድሜ ላይ ብሆንም፣ በቁመቴ ምክንያት ሥራ በማጣቴ የሰው እጅ እየጠበቅኩ ለመኖር ተገድጃለሁ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በ1998 ዓ.ም. ላይ በአካባቢው ወደሚገኝ ትምህርት ቤት የገባው ነጋዎ፤ "ትምህርት ስጀምር በወቅቱ ቁመቴ ያን ያክል ረዥም አልነበረም" ይላል።
". . . ቁመቴ መጨመር የጀመረው ከ2005 ጀምሮ ነው። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ቁመቴ በጣም በፍጥነት መጨመር ጀመረ" ሲል ያስታውሳል።
የ24 ዓመቱ ወጣት ቁመቱ 2.25 ሜትር የደረሰ ሲሆን፣ አሁንም ቁመቱ ከእድሜው ጋር እየጨመረ እንደሆነ ያስረዳል።
"ቁመቴ ከጓደኞቼ በላይ እንደሆነ ስረዳ በየቀኑ መለካት ጀመርኩ። ቁመቴ ከእድሜዬ ጋር አሁንም እየጨመረ ነው" በማለት ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, FIB TV
የሰዎች አስተያየት
ነጋዎ ቁመቱ ከሌሎች የተለየ ከሆነ በኋላ የሰዎች ትኩረት ውስጥ መግባቱን ይናገራል። "ቁመቴ የተለየ ሲሆን ሰዉ ዓይኑን እኔ ላይ አደረገ። በዚህ ምክንያት እኔ ራሴ ለጥቂት ዓመታት እፍረት ይሰማኝ ነበር" በማለት ቁመቱ ያስከተለበትን ተጽእኖ ይናገራል።
"አንዳንድ ሰዎች ቁመቴን በተመለከተ የሚሏቸው ነገሮች ወደ ውጪ ወጥቼ ከጓደኞቼ ጋር እንዳልውል እና እንዳልንቀሳቀስ አድርጎኛል" በማለት ከሰዎች ራሱን በማራቅ ለብቻው መሆን ይመርጥ እንደነበር ያስታውሳል።
በትምህርት ቤት የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ እንደነበረ እና በሕመም ምክንያት ትምህርቱን ከ8ኛ ክፍል ለማቋረጥ ተገዷል።
ወጣት ነጋዎ ተማሪ ሳለ ጭንቅላቱ ላይ እጢ ወጥቶበት በሕመሙ ምክንያት መራመድ አቅቶተት ነበር።
"ያ ሕመም እጅግ በጣም ነው የጎዳኝ። በእግሬ እየተራመድኩ መሄድ እንኳን አቅቶኝ ነበር። 2010 ላይ ሐኪም ጋር ሄጄ ለሁለት ዓመት ሕክምና ስከታተል ነበር።"
ነጋዎ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕምናውን ተከታትሎ ጨርሶ ከወጣ በኋላ በራስ መተማመኑ መጨመሩን እና ይሰማው የነበረው ሃፍረት መቅረቱን ይናገራል።
"ሰዎች ከሚሰበሰቡበት ቦታ ራሴን ማራቅ እና ማፈር ትቻለሁ። . . . ቁጡ እና ብስጩነቴ ቀርቶ አሁን ተረጋግቻለሁ" በማለት ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Nagawo Facebook Page
ወጣት ነጋዎ በቁመቱ ምክንያት በርካታ ማኅበራዊ ፈተናዎች እንዳጋጠሙት ይናገራል። ወጣቱ መስራት ባለመቻሉ በወላጆቹ ድጋፍ ህይወትን እየገባ እንደሆነ ይናገራል።
"ቁመቴ ከልክ በላይ ስለሆነ ሥራ መስራት አልችልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚሆነኝ ጫማ እና ልብስ ማግኘት አልቻልኩም።"
"ልብስ ተለክቼ አሰፍለሁ፤ ጫማ ግን አገር ውስጥ አላገኝም። የጫማ ቁጥሬ 54 ስለሆነ አገር ውስጥ አይገኝም" በማለት በተፈጥሮው ምክንያት የገጠመውን ችግር ያስረዳል።
ነጋዎ ልብስ ሲያሰፋም ሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት ሲጠቀም በሰውነቱ ትልቀት ምክንያት ከሌለው ሰው በተለየ እጥፍ እንዲከፍል ይገደዳል።
"ልብስ ሳሰፋ እጥፍ ከፍዬ ነው የማሰፋው። መደብር ሄጄ ጫማ አማርጬ መግዛት አልችልም። በብዙ ወጪ ነው ከውጪ አገር የማስመጣው። መኪናም ስሳፈር የሁለት ሰው ቦታ ስለምይዝ እጥፍ ነው የሚያስከፍሉኝ" በማለት በቁመቱ ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን ይናገራል።
ነጋዎ ጫማ እና ልብስ የሚሰጡት ግለሰቦች እንዳሉም ጨምሮ ይናገራል።
ነጋዎ ረዥሙ ኢትዮጵያዊ?
"በጣም ረዥም ቁመት ያላቸውን ሰዎች አይቻለሁ። ከእኔ የሚበልጥ ግን እስካሁን አላየሁም። ኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም የተባለው አስራት የሚባል ሰው እንደሆነ ሰምቻለሁ። የእሱን ቃለ መጠይቅ አይቻለሁ። በቃለ መጠይቁ እሱ 2.22 ሜትር እንደሚረዝም ነው የሚናገረው። እኔ ደግሞ ቁመቴ 2.25 ሜትር ነው። አሁንም ቁመቴ እየጨመረ ነው" በማለት ይናገራል።
የወደፊት እቅዱ?
ነጋዎ ዋናው እቅዱ በትምህርቱ መግፋት እንደሆነ ገልጾ፤ ትምህርቱን ካቋረጠበት ከ8ኛ ክፍል መልሶ በጀመር በማታ መርሃ ግብር እየተከታተለ መሆኑን ይናገራል።
"ከትምህርቴ ጎን እውቅና አግኝቼ ባህል እና ቱሪዝም ላይ መስረት እፈልጋለሁ። ሰዎች ቁመቴን ተጠቅሜ ማስታወቂያዎችን እንድሰራ ያበረታቱኛል። እስካሁን ያነጋገረኝ አካል ባይኖርም እድሉን ባገኝ ግን ደስ ይለኛል።"
ነጋዎ በመጨረሻም፤ አምስት እህቶች እና አራት ወንድሞች እንዳሉት በመጥቀስ ቁመታቸው እንደእሱ ረዥም እንዳልሆነ በመጥቀስ ". . . በቤተሰባችን ውስጥ ራሱ ረጅም የሆነ የለም" በማለት የእሱ ቁመት የተለየ ተፈጥሮ ስጦታ እንደሆ ነገዎ ይናገራል።












