ላይቤሪያ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አሮጌ የገንዘብ ኖቶችን አቃጠለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የላይቤሪያ ማዕከላዊ ባንክ ያረጁ እና የተበላሹ የገንዘብ ኖቶችን በአዲስ ለመተካት በሚል አራት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አሮጌ የገንዘብ ኖቶችን አቃጥሏል።
በአገሬውም የመገበያያ ገንዘብም የተቃጠለው 600 ሚሊዮን የላይቤሪያ ዶላር ነው።
የገንዘብ ኖቶቹ እንዲወገዱ የተደረጉትም መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ ኖቶችን ቢያትምም አሮጌዎቹ በስርጭት ላይ ይገኛሉ የሚለውን ስጋት ተከትሎ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2018 ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥት ገንዘብ ጠፍቷል የተባለ ሲሆን እንዲሁም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ አዲስ የታተሙ የላይቤሪያ የገንዘብ ኖቶች ጠፍተዋል የሚል ክስም እየቀረበ ይገኛል።
ማዕከላዊ ባንኩ ይህንን አይቀበለውም የተባለው ገንዘብ በባንክ ካዝና ውስጥ መቀመጡን ገልጿል።
የፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ መንግሥት አሮጌውን የላይቤሪያ ዶላር ለመተካት እና የሀገር ውስጥ ምንዛሬን ለማጠናከር በዚያው አመት ከሀገሪቱ የመጠባበቂያ ሂሳቦች ያወጣውን 25 ሚሊዮን ዶላር እስካሁን አልተካም።
ይህንን ሊቀበሉ ያልቻሉ የተሟጋች ቡድኖች ማብራሪያ እና ተጠያቂነት እንዲኖር እየጠየቁ ነው።
የላይቤሪያ ምጣኔ ኃብት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንገዳገድ ቢያሳይም ነገር ግን ፕሬዚደንት ዊሃ በዚህ አይስማሙም በቅርቡ ለፓርላማ ባደረጉት አመታዊ ንግግር ኢኮኖሚው የተረጋጋና እያደገ ነው ብለዋል።












