በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተበጥሶ የወደቀ የኤሌክትሪክ ገመድ 26 ሰዎችን ገደለ

የገበያው አካባቢ
የምስሉ መግለጫ, የገበያው አካባቢ

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የገበያ ስፍራ የኤሌክትሪክ ኃይል ገመድ ወድቆ ቢያንስ 26 ሰዎች በኤሌክትሪክ ተይዘው መሞታቸውን ፖሊስ ገለፀ።

በአገሪቱ ዋና ከተማ ኬንሻሳ አቅራቢያ ባለ የገበያ ቦታ ላይ ባሉ ቤቶችና ለግብይት በወጡ ሰዎች ላይ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ ከፍተኛ የኃይል ተሻካሚ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ያልተረጋገጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ በርካታ በድን የሰው አካላት በውሃ ላይ ወድቀው ይታያሉ።

ለ25 በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት የሆነው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላላፊያ ገመድ በምን ምክንያት ተቆርጦ እንደወደቀ ግልጽ አይደለም።

የአገሩ ፖሊስ እንዳለው ይህ አሰቃቂ አደጋ የደረሰው ከኬንሻሳ ወጣ ብሎ በሚገኘው ማታዲ-ኪባላ በተባለው አውራጃ ውስጥ በሚገኝ የገበያ ቦታ ሲሆን፣ የአደጋው ሰለባዎች በሙሉ እዚያው ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በገበያው ውስጥ የሚነግዱ ሴቶች ናቸው።

"በጠዋት የጣለውን ዝናብ ተከትሎ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ በርካቶችን ይዞ በዝናብ ውሃ በተሞሉት ጉድጓዶች ውስጥ በመውደቅ ሕይወታቸው አልፏል" ሲሉ የኬንሻሳ ግዛት አስተዳደር ቃል አቀባይ ቻርልስ ምቡታሙቡነቱ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም የአደጋው ሰለባዎች አስከሬን ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ለአደጋው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አንድ በገበያው ውስጥ የሚሰራ ነጋዴ እንደተናገረው ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ አካባቢው በውሃ የሚጥለቀለቅ ሲሆን ገብያተኞች በውሃ ውስጥ እየተዘዋወሩ ነው የሚገዙና የሚሸጡት።