በጊኒ ቢሳው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በርካቶች ሳይገደሉ አይቀርም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጊኒ ቢሳው በተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ሁኔታው በቁጥጥር ነው ያሉ ሲሆን ድርጊቱን "በዲሞክራሲ ላይ የተደረገና ያልተሳካ ጥቃት" ሲሉ ገልጸውታል።
መፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ ለድርጊቱ የመረጡት ፕሬዝዳንቱ በካቢኔ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ የተነገረበትን ወቅት ሲሆን በዋና ከተማው ቢሳው በሚገኝ የመንግሥት ህንጻ አቅራቢያ የተኩስ ልውውጥ ተሰምቶ ነበር።
ወታደሮች ፕሬዚዳንቱን እና ሚኒስትሮችን በቁጥጥር ሥር አውለው እንደነበረም ተገልጿል።
በሙከራው ማንነታቸው ያልተገለጸ ሲቪል የለበሱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው አንድ የፖሊስ አባል መገደላቸውን የደህንነት ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች ድርጊቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ወታደሮቹ ወደ ጦር ሰፈራቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።
ሆኖም በቢሳው የተፈጠረው ነገር በትክክል ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጡት ታጣቂዎች ማንነት እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን ፕሬዚዳንቱም ስለተገደሉት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ይፋ አላደረጉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ላይ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላት እና የቀድሞዋ የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት የነበረችው ጊኒ ቢሳው ከእንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1980 ጀምሮ ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥቶች ወይም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን አስተናግዳለች።
በከፍተኛ የውጭ ብድር እና የውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ ያላት ሀገሪቱ የላቲን አሜሪካ የዕጽ አዘዋዋሪዎች መሸጋገሪያ ሆናለች።
ትላንት ምሽት ፕሬዝዳንት ኢምባሎ "የተዘጋጀው እና የተደራጀው" መፈንቅለ መንግሥት አድርጊው ቡድን "በዕፅ አዘዋዋሪዎች ውስጥ ከተሳተፉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል" ብለዋል። ሆኖም ጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ አልሰጡም።
ትላንት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባቸው ፕሬዝዳንት ኢምባሎ እአአ 2019 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ያሸነፉ ሲሆን ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ከፓርላማ አባላት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር።
በቅርቡ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት በተደጋጋሚ እየታየ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በማሊ፣ ቻድ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች ተካሂደዋል።












