ፑቲን 'አሜሪካ ወደ ጦርነት እንድንገባ እየገፋፋችን ነው' አሉ

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ወደ ጦርነት እንድንገባ እየገፋፋችን ነው ሲሉ ወቀሱ።

የዩክሬን ውጥረት ከተፈጠረ በኋላ የመጀመርያ በተባለ ንግግራቸው ነው ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት።

ፑቲን እንደሚሉት የአሜሪካ ዋና ዓላማ ሩሲያን ወደ ጦርነት በማስገባት በሩሲያ ላይ ተደራራቢ ማዕቀብ እንዲጣል ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።

ፑቲን ከዚህ አስተያየት በተጨማሪ አሜሪካ የኔቶ ጥምረት ሩሲያን ሊያሳስባት እንደሚችል ለመረዳት አልፈቀደችም ብለዋል።

ካለፉት ሳምንታት ወዲህ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ድንበር እየተጠጉ በመምጣታቸው ከዛሬ ነገ ሩሲያ ጎረቤቷን በኃይል ትወራለች የሚለው ስጋት እያየለ መጥቷል።

ሩሲያ በቅርብ ሳምንታት እስከ 100ሺህ ሠራዊት ወደ ድንበር ሳታስጠጋ አልቀረችም።

ታንክና ከባባድ የጦር መሣሪያ የጫኑ ካሚዮኖችም በብዛት ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ላይ ተሰልፈዋል ተብሏል።

ያም ሆኖ ሩሲያ ምዕራባዊያን ስሜን እያጠፉት ነው እንጂ እኔ አንዳችም የወረራ ሐሳብ አልጠነሰስኩም ትላለች።

ሩሲያ በተመሳሳይ የዛሬ 8 ዓመት ገደማ የዩክሬን ደቡባዊ ባሕረ ገብ ክሪሚያን ወደ ራሷ መልሳ ማስገባቷ ይታወሳል።

ሞስኮ በተቃራኒው የዩክሬን መንግሥት በምሥራቁ ክፍል ሰላም ማስከበር ተስኖታል ስትል ትወቅሳለች።

በምሥራቅ በኩል 14ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሩሲያ የሚደገፉት አማጺያን ሰፊውን ግዛት ያሰተዳድራሉ።

ይህ በእንዲህ ሳለ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚየር ዘሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጦርነቱ የሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን የመላው አውሮጳ ጦርነት ነው የሚሆነው ብለዋል።

ፑቲን በበኩላቸው አሜሪካ የሩሲያን ዕድገት በአጭር ለመቅጨት ዩክሬንን እየተጠቀመችባት ነው እንጂ አሜሪካ የዩክሬን ጉዳይ አሳስቧት አያውቅም ሲሉ ከሐንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ፕሬዝዳንታዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በአሜሪካና በሩሲያ መካከል የጦር መሣሪያ ፉክክር የተጀመረው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በተለይም በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።

ይህም እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ከ1947 እስከ 1989 ዓ/ም የዘለቀ ነው።

በዚያን ዘመን ዩክሬን የታላቋ ሶቭየት ኅብረት አንድ አካል ነበረች።

አሁን በዩክሬን ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን 'ፑቲን በዩክሬን ጭንቅላት ላይ ሽጉጥ የደገኑ መሪ ናቸው' በማለት ጠንካራ አስተያየት ሰጥተዋል።

ጆንሰን ጨምረውም ክሬምሊን ጠብ ከማጫር እንድትቆጠብም ተማጽነዋል።

በጉብኝታቸው ቦሪስ ጆንሰን ለዩክሬን 119 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል። ይህም ገንዘብ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን እና ዩክሬን በኋይል ራሷን እንድትችል ለማገዝ ነው ብለዋል።

ቦሪስ ጆንሰን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የኃይል እርምጃ ብትወስድ ማእቀብ እናዘንብባታለን ሲሉ ዝተዋል።