'የኢትዮጵያ ታንብብ' መስራቹና የንባብ ጀግናው ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ ማን ነበሩ?

የፎቶው ባለመብት, Glenn Asakawa
ጥር 10/2014 ዓ.ም ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትና በአንድ ወቅት 'የሲኤን ኤን ጀግና' [CNN HERO] ለመባል የበቁት ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ በርካቶች የሚያስታውሷቸው በአህያ የሚጎተት ቤተ መጻሕፍት በማቋቋማቸው ነው።
አቶ ዮሐንስ በወቅቱ፣ በህጻናትና ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመሥራታቸው ከፍተኛ አድናቆት ተቸሯቸዋል።
በተለይም በአህያ የሚጎተት ቤተ መጻህፍት የማቋቋም ሐሳባቸው ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ አድርጓቸው ነበር።
በአገር ውስጥ የተለያዩ ሽልማቶችና ዕውቅናዎች ከማግኘታቸው በተጨማሪ በአሜሪካ ከሚገኘው ሪጅስ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክተርነት ማዕረግ እስከማግኘት ደርሰዋል።
የሲኤንኤን ቴሌቪዝን ጣቢያም ከመላው ዓለም 'የሲኤን ኤን ጀግኖች' በሚል ከተለያዩ መስኮች ከሚመጣታቸው ምሳሌዎች መካከል አንዱ ለመሆንም ችለው ነበር።
ምልሰት ወደ ልጅነት
አቶ ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ በ1940 ዓ.ም መግቢያ ላይ ነገሌ ቦረና በተባለች ትንሽ ከተማ እንደተወለዱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲሁም ቃለ-መጠይቆች ላይ ይገልጹ ነበር።
አቶ ዮሐንስ በሕይወት ዘመናቸው በሰጧቸው ቃለ መጠይቆች "በዚያች ከመንደር የማትበልጥ ትንሽዬ ከተማ፣ ነገሌ ቦረና ነው የተወለድኩት። ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ጀመርኩ። በምማርበት ትምህርት ቤት ግን መጽሐፍ የሚባል ነገር አልነበረንም" በማለት ስላሳለፉበት ሁኔታ ይናገራሉ።
አቶ ዮሐንስ ገና ብላቴና ሳሉ በትምህርት ቤታቸው ለማንበብ ቢፈልጉም ዓይናቸውን ከንባብ የሚያዋድድ፣ ለተማሪው የቀረበ የመጻሕፍት ዘር ማግኘት አስቸጋሪ ነበር።
ስድስተኛ ክፍል ሲደርሱ ግን በጣት የሚቆጠሩ የትምህርት መማሪያ መጻሕፍት ማግኘት ቻሉ። ከዚያም ንባብ እና አቶ ዮሐንስ እንደ አንድ እናት ልጆች ተዋደው እና ተጋምደው ኖሩ።
ከስምንት ዓመታት በፊት ቴድኤክስ አቴንስ [TEDxAthens] ባዘጋጀው መድረክ ላይ "ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል ከመጻሕፍት ጋር ያለኝ ፍቅርና ቁርኝት ይበልጥ የጸና መሆን የጀመረው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
የ19 ዓመት ወጣት በነበሩበት ወቅትም አንድ ከአሜሪካ የመጣ ቤተሰብ በርካታ መጻሕፍት ይዞ መጣ።
ለያኔው ብላቴና ተማሪ ዮሐንስ፣ ይህ መልካም አጋጣሚ ነበር።
ዮሐንስ እንዚህን መጽሐፍት መዋስ ይችሉ እንደሆን ላቀረቡት ጥያቄ መልካም ምላሽ በማግኘታቸው፣ በፈረንጅ አፍ የተጻፉትን መጻሕፍት ለማንበብ በቁ።
አቶ ዮሐንስ የንባብ ፍላጎታቸው እና ልምዳቸው እንዴት እንዳደገ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተጠይቀው ሲመልሱ "የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በወቅቱ ወደነበረው የባሕር ኃይል ተቀላቀልኩ። በማሰልጠኛ ማዕከሉም በሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ላገኝ ቻልኩ። ሳላማርጥም የተለያየ ይዘት ያላቸውን ማንበብ ጀመርኩ" ሲሉም በትውስታ የተናገሩበት አጋጣሚ ነበረ።

የፎቶው ባለመብት, Yohannes FB page
አቶ ዮሐንስ በ1980ዎቹ ከአገር በመውጣት ኑሯቸውን አሜሪካ አደረጉ። በዚያም የላይብረሪ ሳይንስ በማጥናት የሁልጊዜም ሕልማቸው ወደነበረው የመጻሕፍት ዓለም ሰተት ብለው ገቡ።
ወደ መጻሕፍት ባሕር . . .
አቶ ዮሐንስ በላይብረሪ ሳይንስ ከተመረቁ በኋላ በአንድ ግዙፍ ቤተመጻሕፍት ተቀጥሮ የመስራት ዕድል አጋጠማቸው።
ለተወሰነ ጊዜ ከሰሩ በኋላም አንድ ነገር ማስተዋል ቻሉ። በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ከ70 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የተጻፉ ስዕላዊ መጻሕፍት ቢኖሩም አንድም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፈ ሊያገኙ አልቻሉም።
በዚያ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ "ለምን ከኢትዮጵዮጵያ ቋንቋዎች በአንዱ የተጻፈ መጽሐፍ ይታጣል?" ብሎ መጠየቅ የማይታሰብ ቢሆንም፤ አቶ ዮሐንስ ግን ይህንን ጥያቄ በማንሳት ብቻ ሊያልፉት አልወደዱም።
ጥያቄውን ለቤተ መጻሕፍቱ አስተዳደር በማቅረብ 1200 ዶላር በጀት ተመድቦላቸው የኢትዮጵያ መጻሕፍት ገዝተው ወደ ቤተ መጻሕፍቱ እንዲያስገቡ ተፈቀደላቸው።
ይህ አነስተኛ ገንዘብ መጻሕፍትን ከኢትዮጵያ ገዝቶ ወደ አሜሪካ ለማጓጓዝ እና በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እንዲገኝ ለማድረግ ስለማይበቃ የራሳቸውን ጽፈው ለማሳተም ወሰኑ።
ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላም "Silly Mamo" በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ጽፈው ለህትመት አበቁት። በኋላም ይህ መጽሐፍ 'ማሞ ቂሎ' በሚል በአማርኛ ተተርጉሞ ለአንባቢ ቀርቧል።

የፎቶው ባለመብት, Yohannes FB page
"ኢትዮጵያ ታንብብ"
አቶ ዮሐንስ ህጻናት እና ወጣቶች በትምህርት ቤቶች የሚቀርቡላቸውን መማሪያ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ መጽሐፍት ማንበብ እንዳለባቸው ጽኑ እምነት ነበራቸው። ለዚህም ነበር በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ የኅብረተሰቡ ክፍል ላይ ትኩረት በማድረግ ለመስራት የመረጡት።
"ህጻናት ከሌሎች ባህሎች፣ ሰዎች፣ ከሌሎች ህጻናትና ከሰፊው ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊጎለብት የሚችለው ከሚያነቡት መጽሐፍ መሰረት በማድረግ ነው" ይሉ ነበር አቶ ዮሐንስ።
"ማሞ ቂሉ" [Silly Mamo] ከተባለው መጽሐፋቸው ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብና በእገዛ ያሰባሰቡትን በመያዝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1998 "ኢትዮጵያ ታንብብ" [Ethiopia Reads] የሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ።
በዚህ አትራፊ ባልሆነ ድርጅት በሚያደርጉት እንቅስቃሴም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቤተ መጻሕፍት የሚሆኑ መጻሕፍት ማሰባሰብ ጀመሩ።
አቶ ዮሐንስ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ያወቀው ተቀጥረው ሲያገለግሉበት የነበረው የሳንፍራንሲስኮ ቤተ መጽሕፍትም ሠራተኛውን ባዶ እጃቸው ሊልካቸው አልፈለገም።
15 ሺህ መጻሕፍት በልገሳ አበረከተላቸው። የተበረከቱላቸውን መጻሕፍት በመያዝ ኢትዮጵያ የገቡት አቶ ዮሐንስ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቤተ መጻሕፍት ለመቋቋም በቁ።
የአቶ ዮሐንስ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት መምህር፣ ደራሲና ተርጓሚ ብርሃነ አቻሜ "ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ነው ቤተ መጻሕፍት የከፈተው። የከፈተው ቤተ መጻሕፍትም ለህጻናትና ወጣቶች የሚያገለግል ነበር" ይላሉ።
"ኢትዮጵያ ሪድስ" በሚለው እንቅስቃሴያቸው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የከፈቱት ቤተ መጻሕፍት በአጭር ጊዜ ከፍተኛ እውቅና በማግኘቱ በርካታ ሰዎች በመሄድ መገልገል ጀመሩ። ክፍሎቹ በመጥበባቸውን ግቢያቸው ውስጥ ድንኳኖች በመትከል አገልግሎት አስከመስጠት ደርሰው ነበር።
አንድ ወቅት ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ላይ "ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የወሰንኩት ህጻናትና ወጣቶች ነገ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራቸው ለመርዳት በማሰብ ነው" በማለት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yohannes FB page
በአህያ የሚጎተተው ቤተመጻሕፍት
አቶ ዮሐንስ ባቋቋሙት 'ኢትዮጵያ ሪድስ' የተባለው አትራፊ ያልሆነ ድርጅት በኩል የተለያዩ መጻሕፍት በመግዛትና በእርዳታ በማሰባሰብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ድጋፍ አድርገዋል።
ለቤተ መጻሕፍት መጻሕፍት በማቅረብና ቤተመጻሕፍት በመገንባት ከሚያደርጉት በጎ ሥራ በተጨማሪ አንድ ለየት ያለ ሃሳብ ወደ ተግባር ሲያሸጋግሩ በመታየታቸው ብዙዎችን አስገርሟል። የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃንም ስለጉዳዩ ዘግበዋል።
የሐሳቡ መነሻ በዚምባቡዌ በነበራቸው ቆይታ የታዘቡት ነገር ነበር። በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት መገንባት በማይቻልባቸው የገጠር አካባቢዎች በአህያ የሚጎተት ቤተ መጻሕፍት በመገንባት ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ የሚል ነበር ውጥኑ። ተግባራዊም አደረጉት።
"አህያ በማኅበረሰባችን በተለይም በገጠሩ አካባቢ ከፍተኛ ቦታ ያለው እንስሳ ነው። የተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚሰጡና በብዛት ስለሚገኙ ነው ተንቀሳቃሹን ቤተ መጻሕፍት እየጎተቱ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረግኩት" ሲሉ 'ቴድኤክስ አቴንስ' [TEDxAthens] ባዘጋጀው መድረክ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ህጻናት በትምህርት ቤቶች ከሚቀርቡላቸው የመማሪያ መጽሕፍት በተጨማሪ ሌሎች መጻሕፍቶችም ማንበብ እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ በአህያ በሚጎተቱ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍቶቻቸው በኩል የተለያየ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን አቅርበዋል።
"ትግራይ ታንብብ ትግራይ ታብብ"
ከ13 ዓመታት በፊት ከታዲያስ አዲስ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ከ2002 እስከ 2009 በነበሩት ዓመታት ውስጥ ለ16 ትምህርት ቤቶች ቤተመጻሕፍት ማስገንባት እንደቻሉ ገልጸው ነበር።
የተለያዩ የህጻናት መጻሕፍት ለህትመት ከማብቃታቸው በተጨማሪ፣ በእነዚያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ መጻሕፍት እንዳከፋፈሉም ተናግረዋል።
"ህጻናት መጽሐፍ በሚገባ አግኝተው በእውቀት እንዲታነጹ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው" በማለት ስለአቶ ዮሃንስ የሚናገሩት መምህር ብርሃነ፣ በ2002 ዓ.ም ወደ ትግራይ በመሄድ ለተለያዩ የትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት በርካታ መጻህፍት በእገዛ ማበርከታቸውን ያስታውሳሉ።
ለትምህርት ቤቶቹ ካደረጉት የመጻሕፍት እገዛና በአህያ የሚጎተት ቤተ መጻሕፍት ከማቅረባቸው በተጨማሪ የመቀለ ከተማ ወጣቶችና ህጻናት የሚገለገሉበት 'ሰገናት' የተባለውን የሕዝብ ቤተመጻሕፍት አቋቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yohannes FB page
እውቅናና ሽልማት
"በሲ ኤን ኤን ጀግኖች ሽልማት ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በዕጩነት ቀርበው ነበር። በመጨረሻ ማሸነፍ የቻሉት ግን 10 ሰዎች ነበሩ። አቶ ዮሐንስም ከአሸናፊዎቹ መካከል ለመሆን በቅተዋል" ይላሉ መምህር ብርሃነ አቻሜ።
ከዚህ በተጨማሪም "ሲሊ ማሞ" በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሐፍ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ላይ 'የአፍሪካ ምርጡ የህጻናት መጽሐፍ' ለመባል በቅቷል። ሽልማቱ አሜሪካ ውስጥ የሚዘጋጅ ሲሆን በአፍሪካውያን ለሚጻፉና ለሚዘጋጁ የህጻናት መጽሐፍት የሚሰጥ ነው።
አቶ ዮሐንስ በአሜሪካው የቤተመጻሕፍት ማኅበርም የክብር አባል ነበሩ።
አቶ ዮሐንስ ከ'ማሞ ቂሉ' [Silly Mammo] የሕጻናት መጽሐፍ በተጨማሪ፣ 'ትርሐስ አሸንዳ ታከብራለች' ['Tirhas celebrates Ashenda'] የሚል መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል።














