ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት ያሉ እድሎችና ተግዳሮቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP
በትግራይ አማፂያን ላይ ድል መቀዳጀቱ የሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ወደ ትግራይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዕቅድ እንደሌለውና በያዛቸው ቦታዎች ተወስኖ እንዲሚቆይ ካሳወቀ ሰነባብቷል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው፣ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ላስከተለው የእርስ በርስ ጦርነት የሰላም ዕድል ለመስጠት በሚል ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ጠቅልለው መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፋር ክልላዊ መንግሥት የህወሓት አማፂያን በሰላማዊ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን እና የተወሰኑ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን አሳውቋል።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት አማፂያን የሚያደርጉትን ትንኮሳ ለመከላከል የመከላከያ እና የክልል ፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በትግራይና በተለያዩ አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች መኖራቸው የሚገጸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እና ሊተነበይ የማይችል እንደሆነ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች አንዱ ወገን የሌላውን የማድረግ አቅም ለማደከም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን በሁለቱም በኩል በጦርነት የመቀጠል ፍላጎታቸው መቀነሱን ያስረዳሉ።
ያገረሹ ግጭቶች
የትግራይ ኃይሎች ከሁለቱም ክልሎች መውጣታቸው የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ወደ ትግራይ ክልል አልዘልቅም ማለቱ በተወሰነ ደረጃ ጦርነቱ ረገብ እንዲል አድርጎታል።
በአንዳንድ ድንበር አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት ግን ተጨማሪ ስጋት እያስከተለ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያነሱታል።
"የሰላም ምልክት ያለ ቢመስልም አሳሳች ድምዳሜ ላይ መድረስ ግን አይገባም። ምክንያቱም ጦርነቱ ረገብ ቢልም፣ በአንዳንድ የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያ የቀጠለበት ሁኔታ አለ። በአላማጣ፣ በማይ ጸብሪና በዓዲ ዓርቃይ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መካሄዱን ሰምተናል" ይላሉ የክራይስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዊልያም ዴቪሰን።
ከዊሊያም ዴቪሰን ሃሳብ ጋር የሚስማሙት የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በአንዳንድ የድንበር አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ የሚያጨልም እንዳይሆን ስጋት እንደሆነ ይናገራሉ።
"ግጭቱን ማነው ያስነሳው የሚለው ለማወቅ ከባድ ነገር ቢሆንም፣ በትግራይ ኃይሎች በኩል ግን ወደ ሰላም ድርድር መግባታችን ስለማይቀር በምንችለው መጠን አቅሙን እናዳክመው የሚል እሳቤ ሊኖር ይችላል" ሲሉም ያክላሉ።
"ያም ሆነ ይህ በሁለቱም በኩል በጦርነት ዓላማቸውን ለማሳካት ያለው ፍላጎት የቀነሰ ይመስላል። ሁለተኛው ነገር ስምምነት ላይ እስኪደረስ በቻሉት መጠን አንደኛው የሌላኛውን አቅም የማዳከም ጥረት እያደረጉ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።'"
እስከ አሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል የተሰማ ነገር ባይኖርም የሰላም ዕድል መኖሩን ግን ዶክተር አደም ይገልጻሉ።
"ድምዳሜ ለመስጠት ልንቸኩል አይገባም። ምክንያቱም በትግራይ በኩል አንድ ድርጅት ነው ያለው፤ በፌዴራል በኩል ግን ብዙ ተሳታፊዎች አሉ፣ ብዙ ፍላጎቶች አሉ። በፓርቲቹ በኩል የአስተሳሰብም የአካሄድም ልዩነትም አለ" በማለት አደም (ዶ/ር) ሁኔታውን ያስረዳሉ።
የሰላምጭላንጭል
ዊልያም ዴቪሰን ሁኔታው በሁለቱም ወገኖች መካከል የሰላም ፍላጎት እንዳለ የሚያመለክት ሁኔታ መኖሩን ያምናሉ።
ከማሳያዎቹም "የትግራይ ኃይሎች ከአፋርና ከአማራ ክልሎች መውጣታቸው አንዱን የፌዴራል መንግሥት ፍላጎት አሟልቷል ማለት ይቻላል።"
የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች አላማቸውን በጦርነት ለማሳካት ያላቸውን ፍላጎት እየተዉ መምጣታቸውን ያስረዳሉ።
"የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ አለመግባት፣ የትግራይ ኃይሎች ደግሞ ተገድደውም ይሁን ፈቅደው ወደ ኋላ መመለሳቸው፤ ሁለቱም 'የምንፈልገውን ዓላማ በጦርነት ብቻ እናሳካለን የሚለውን ነገር ያቆሙ ይመስለኛል" ይላሉ።
ዊሊያም አክለውም የትግራይ አማፂያን ከአማራ እና ከአፋር ክልል መውጣታቸውን ተከትሎ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተባበሩት መንግሥታት በጻፉት ደብዳቤ፤ የአማራ እና የኤርትራ ኃይሎች ከምዕራብ ትግራይ እንዲወጡና እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸው፣ በትግራይ አመራር በኩል የአስተሳሰብ ለውጥ መኖሩ የሚያመላክት ነው ይላሉ።
እንዲሁም፣ በፌዴራል መንግሥት በኩል የተቃውሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር እና አባል የሆኑ እሰረኞቹን መፍታቱ በአገሪቱ ያለው ቀውስ በሰላማዊ ድርድር እንዲያልቅ ፍላጎት እንዳለ የሚሳይ መሆኑን ይናገራሉ።
አደም ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው "በሥርዓትና ይፋዊ በሆነ መልኩ የተኩስ ማቆም ስምምነት እስካልታወጀ ድረስ ያለው ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም" በማለት ያለውን የታየውን ለውጥ ይገልጹታል።
"በእኔ እምነት ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል የፌዴራል መንግሥቱ የአየር ላይ ጥቃት እያካሄደ ያለው፤ ከመደራደራችን በፊት በተቻለ መጠን የትግራይ ኃይሎች የመደራደር አቅም ማዳከም አለብን የሚል እሳቤ ያለ ይመስለኛል" ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስጋቶችና እንቅፋቶች
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን እንደደደረሰ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ከትግራይ ለቅቆ ቢወጣም ክልሉ "ይፋዊ ባልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ" ውስጥ በመሆኑ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የማቅረቡ ሥራ አስቸጋሪ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ምንም አይነት እቀባ አለማድረጉን ቢገልፅም፣ በክልሉ የሚገኙ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ቢሆኑም ከመድኃኒት እና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ውጪ መሆናቸውን በመጥቀስ በቀላል ሕክምና የሚድኑ ሕሙማን ህይወታቸውን እያጡ መሆኑን ይናገራሉ።
በቅርቡም በአፋር ክልል በአባላ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ማለፍ አለመቻላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ገልጸዋል።
ዊልያም ዴቪሰን በአጭር ጊዜ የሰላም ድርድር ካልተጀመረ የትግራይ ኃይሎች ይህንን 'የሰብዓዊ እርዳታ ዕቀባ' ለማስከፈት እና የትግራይ ክልልን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ በተለይ በምዕራብ ትግራይ ጦርነት መክፈታቸው አይቀርም ይላሉ።
"የትግራይ ኃይሎች ወደ ኋላ ሲመለሱ ብዙ ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል" የሚል ግምት ያላቸው ዳቪሰን፣ አሁንም ድረስ ግን ከፍተኛ የጦር ኃይል እንዳለቸው ያምናሉ።
"የትግራይ ኃይሎች በማናቸውም መመዘኛ አሁንም ከፍተኛ ጦር ነው ያላቸው። እነርሱ ሕዝባቸው ላይ ተከፍቶበታል ከሚሉት 'የዘር ማጥፋት' ዘመቻ ለመከላከል የህልውና ትግል እያደረጉ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ።"
በተጨማሪም "አዲስ አበባ እና አሥመራ ያሉት መንግሥታት ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ለራሳቸውና ለሕዝባቸው ዋነኛ ስጋት አድርገው ነው የሚመለከቷቸው" ይላሉ ዴቪሰን።
ይህ በሁለቱም ወገን ያለው አመለካከት ደግሞ ለሚታሰበው የሰላም ሂደት "ከባዱ እንቅፋቱ" ሊሆን እንደሚችልና "በመካከላቸው ካለው አለመተማመንና መጠራጠር አንጻር የትግራይ ኃይሎች ሠራዊታቸውን ለመበተን የሚስማሙ አይመስለኝም" ይላሉ።
አደም (ዶ/ር) በበኩሉ፣ በተለይ በአፋርና በአማራ ክልል በኩል ጦርነቱ በሰላም የማያልቅ ከሆነ መልሶ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተጨባጭ ስጋት እንዳለ ይገምታሉ።
በትግራይ በኩልም፣ የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ ክልል ገፍቼ 'አልሄድም' ቢልም ጥርጣሬዎች እንደሚፈጠሩ ያስገነዝባል።
ለዚህ ደግሞ "በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልል አንዳቸው ወደሌላኛው በኩል ዘልቆ የመግባት ዕቅድ እንደሌላቸው ሁሉም ማሳየት አለባቸው።"
የእስረኞች መፈታት
በቅርቡ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለን ገርባ እንዲሁም አቶ እስክንደር ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከእስር ተፈትተዋል።
ዊልያም ዴቪሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወሰዱት እሰረኞችን የመፍታት እርምጃ፣ በተለይ ሊካሄድ ለታቀደው አገራዊ ውይይት አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ያምናሉ።
አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ስድስት ነባር የህወሓት አመራሮች መፈታታቸውን በተመለከተ ግን "እምብዛም ፖለቲካዊ ትርጉም የለውም" ይላሉ ዴቪሰን።
"እነዚህ የህወሓት የፖሊት ቢሮ አባላት ያልሆኑትን መፍታት እንደ ትልቅ ጉዳይ አድርጌ አላየውም፤ ሰላማዊ ድርድር እንዳይደርግ እንቅፋት የሆኑት ጉዳዮችን ከመቀነስ አንጻር፤ እምብዛም ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ መስሎም አይታየኝም።"
ይህ ብቻ ሳይሆን ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአሸባሪነት መዝገብ መስፈራቸው ለሚደረጉ የሰላም ንግግሮች እና ድርድሮች እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ሁለቱም ተንታኞች ይስማማሉ።
ድርጅቶቹ ከዚህ ፍረጃ ካልወጡ በስተቀር፣ የሰላም ድርድር እንዳይደርግ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም እዚህም እዚያም ይደመጣል።
ይህንን በተመለከተ ዊሊያም ዴቪሰን፣ ድርጅቶቹ ከዚህ ፍረጃ ወጥተው፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ፣ የአገር አቀፍ መድረኩ ውስጥ እንዲሳተፉ ካልተደረገ፣ አገራዊ ውይይቱ ውጤት አያመጣም የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ።
ማምለጥ የሌለበት ዕድል
የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት እንዲሁም አገራት ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች ተዛምቶ ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት በሰላማዊ መገድ እንዲፈታ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሻክሮ የነበረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት መሻሻል ሰላም ለማውረድ አዎንታዊ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል።
ዊልያም ዴቪሰን የሰላም ሂደቱ ውጤት እንዲያመጣና ጦርነቱ እንዲቆም ግን በተለይ በትግራይ ያለውን 'የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ' በአስቸኳይ መፈታት አለበት ይላሉ።
"ሁለቱም ወገኖች የሰላም ዕድሉ ሊያመልጣቸው አይገባም" የሚሉት ዳቪሰን፤ ስልክ፣ መብራትና ባንክን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች መከፈት እንዳለባቸው እንደ መፍትሄ ሃሳብ ያቀርባሉ።
አደም ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የምዕራብ ትግራይን ጉዳይ በማንሳት በሁለቱም የፖለቲካ ተፋላሚ ወገኖች በኩል "አስቸጋሪ የፖለቲካ ጭቅጭቅ" ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
"ሁለቱም ወገኖች ቢያንስ የሕግ ሥርዓቱን መከተል አለባቸው" ነገር ግን ችግሩ የመጨረሳውን ዕልባት የሚያገኘው በፖለቲካዊ መንገድ በመሆኑ ይህም ወደተሻለ መተማመን እንደሚያደርስ በመግለጽ ሃሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።













