በሰሜን ኢትዮጵያ የከፋ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ

የምግብ ሳህን የያዙ ልጆች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ የከፋ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቀቀ።

ድርጅቱ ባካሄደው ግምገማ በትግራይ 40 በመቶ የሚጠጉሰዎች በከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ ሲሆኑ፣ በጦርነቱ በተጎዱ በሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በአጠቃላይ ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

በትግራይ በተደረገው አስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዋስትና ግምገማ 83 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የምግብ ዋስትና ችግር አጋጥሞታል ተብሏል።

በዚህም ሳቢያ ቤተሰቦች ያላቸውን ምግብ ሁሉ አሟጠው በመጨረሳቸው ጥራጥሬ ብቻ መመገብና የሚመገቡትን የምግብ መጠንን ለመቀነስ መገደዳቸው ተገልጿል።

ከተመጣጣነ ምግብ አንጻር ግምገማው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 13 በመቶው እና ከነፍሰጡር ሴቶች ግማሽ ያህሉ እንዲሁም ጡት የሚያጠቡ እናቶች ለተለያዩ ችግሮች በሚያጋልጥ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ ችግር ገጥሟቸዋል ብሏል።

በአጎራባች የአማራ ክልልም በቅርቡ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ባለፉት አምስት ወራት የረሃብ ሁኔታ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

በዚህም ሳቢያ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል 14 በመቶው እንዲሁም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች የተመጣጣነ ምግብ ችግር አጋጥሟቸዋል።

በአፋር ክልል ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት በተከሰቱ መፈናቀሎች ምክንያት ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ ችግር መጠን ከፍ ብሏል።

በቅርቡ የተሰበሰበ መረጃ እንዳመለከተው በክልሉ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል 28 በመቶው የተመጣጠነ ምግብ ችግር አጋጥሟቸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአማጺያን ጋር እያካሄደው ያለው ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ወደ ተቀሰቀሰባት የትግራይ ክልል የረድኤት ድርጅቶች የእርዳታ ለማቅረብ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟቸው መቆየቱ ተነግሯል።

ምንም እንኳን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ሊከሰት የሚችልን ረሃብ ለመከላከል በየቀኑ የእርዳታ አቅርቦት የያዙ 100 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደክልሉ መግባት ቢኖርባቸውም ካለፈው ታኅሣሥ ወር አጋማሽ ወዲህ ምንም አይነት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ለመሄድ አልቻሉም ተብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው በተጀመረው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ውስጥ በሙሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ከ9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አመልክቶ፤ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች የእርዳታ አቅርቦት እንዲጓጓዝ እንዲፈቅዱ ጠይቋል፥።

ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚያካሂደው የእርዳታ አቅርቦት 337 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።