አሜሪካ በአፋር ክልል አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ እንዳሳሰባት ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ በአፋርና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ አሳስቦኛል አለ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ሐሙስ ጥር 18/2014 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "በአፋር ክልል ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀሱ እጅግ አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
ከቀናት በፊት የህወሓት ኃይሎች ከትግራይ ክልል አዋሳኝ የሆኑ በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
የህወሓት ኃይሎች ደግሞ ከአፋር ኃይሎች በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰኞ ጥር 16/2014 'ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ' መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው፤ የአሜሪካ መንግሥት ግጭት እንዲቆም እና በሁሉም አካላት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከ ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቃል አቀባዩ፤ ጦርነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ደኅንነት እና ፀጥታ ስጋት መሆኑን በመጥቀስ፣ በግጭቱ አካባቢ ላሉ ሰዎች ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች እና ግጭቱ በድርድር እንዲጠናቀቅ የመንግሥታቸው ፍላጎት መሆኑን አመልክተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ኔድ ፕራይስ ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ላለፉት ሦስት ወራት ያህል በመላው አገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉ የአሜሪካ መንግሥት በበጎ እንደሚመለከተው ገልጸዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ጥር 17/2014 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ያሳለፈው ውሳኔ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል።
"ይህ ውሳኔ [የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ መወሰኑን] በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ብለን ተስፋ እንዳርጋለን" ሲሉ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ በበርካታ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች በሚካሄድበት ወቅት ነበር በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል በሚል ነበር ሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት ወር ማጠናቀቂያ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው።
ኔድ ፕራይስ ጨምረውም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት ሰዎች እንዲፈቱም በመግለጫቸው ጠይቀዋል።
ቃል አቀባዩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም የሚቻለው በድርድር ግጭት ሲቆም፣ የታሰሩ ሰዎች ሲፈቱ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ሲፈቀድ እና ሁሉን አካታች የሆነ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ መሠረት ሲጣል ነው ብለዋል።
አሜሪካ በትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች የተዛመተው ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት ከአማጺያኑ ጋር ድርድር አድርጎ ጦርነቱ እንዲቋጭ ግፊት ስታደርግ የቆየች ሲሆን፣ ልዩ መልዕክተኛ ሰይማም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣንት ጋር ውይይት ሲደረግ ቆይቷል።














