ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥሪ አቀረበ።
ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቡዕ ጥር 18/2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በመላው አገሪቱ ከጥቅምት 25/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያበቃ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው።
ይህ ለሦስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ አበረታች እርምጃ ነው ሲል ኢሰመኮ አድናቆቱን ገልጿል።
ጨምሮም በአገሪቱ ካቢኔ የተላላፈውን ውሳኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአፋጣኝ ተመልክቶ እንደሚያጸድቀው ኮሚሽኑ ተስፋውን የገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላትም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ አሁንም በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችን በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ኢሰመኮ ጨምሮም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ መሆኑን ከሚያጸድቅበት ቀን ጀምሮ ከእስር ያልተለቀቁ ሰዎች የሚኖሩ ከሆነ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው አሳስቧል።
ይህ ካልሆነ ግን እስሩ ከሕግ ውጭ ስለሚሆን የሁሉም የሕግ አስከባሪ አካላት የሕግ ማስከበሩን ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲያከናወኑ ም ጠይቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ የነበረው ሁኔታ በመሻሻሉና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት የአዋጁ አስፈላጊነት እየተገመገመ ተገቢው ማሻሻያ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም በአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነ አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ያወጀ ሲሆን፣ ይህ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን የህልውናና አደጋን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የነበረውን ስጋት በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ከሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ አቀርቧል።
በዚህም ምክንያት ይህ የውሳኔ ሐሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ሲጸድቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ የተወሰኑ ነገሮች ቀሪ ሆነው መደበኛው የሕግ ሥርዓት ይተገበራል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቁጥጥር ስር ውለው መቆየታቸው ሲነገር የቆየ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ስለታሳሪዎቹና ስላሉበት ሁኔታ ስጋቱን በመግለፅ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገ በኋላ በቁጥጥር ስር ከቆዩት ግለሰቦች መካከልም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጀምሮ የተወሰኑት እየተለቀቁ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ መሆናቸው ይነገራል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ወደ አዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትሮች በተቃረበበት ወቅት ነበር።














