የህወሓት ኃይሎች ሦስት የአፋር ወረዳዎችን መቆጣጠራቸው ተገለጸ

የአፋር ልዩ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የምስሉ መግለጫ, የአፋር ልዩ ኃይል አባላት

የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ኃላፊው አቶ አቶ አህመድ ካሎይታ የህወሓት ኃይሎች ባለፉት ጥቂት ቀናት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመክፈት በዞን ሁለት ስር በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ላይ ወረራ ፈጽመዋል ብለዋል።

ባለፉት ሳምንታት በትግራይ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ድንበር ላይ ለተከሰተው ጦርነት አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ትናንት ጥር 16/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የህወሓት ኃይሎች አብአላ፣ መጋሌ እና በራህሌ ወረዳዎች ላይ ጦርነት ከፍተዋል ብሎ ነበር።

ህወሓት በበኩሉ የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታን ለማደናቀፍ በአፋር በኩል ያለውን ጦርነት እየተጠቀመበት ነው ያለ ሲሆን፣ የኤርትራና የአፋር ክልል ኃይሎች በአብአላ በኩል ጦርነት እንደከፈቱና ይህም ሆን ተብሎ የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎችን ለማገድ ሰበብ እንዲሆን ነው ብሏል።

በተጨማሪ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ስለያዟቸው አካባቢዎች በውጭ ግንኙነት በኩል ማክሰኞ ዕለት በወጣው መግለጫ ለሳምንታት ከአፋር ኃይሎች በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰኞ ጥር 16/2014 ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

በመግለጫው ላይ የመንግሥት አጋር በሆኑት በአፋር ክልል ኃይሎች "የተደቀነውን ስጋት ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ተገደናል" ያለ ሲሆን፣ ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል ውስጥ የመቆየትና ግጭቱን የማባባስ ፍላጎት እንደሌላቸው አመልክቷል።

አቶ አሕመድ በህወሓት ኃይሎች ወረራ የተፈጸመባቸው ወረዳዎች ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ መሆናቸው አስታውሰው፤ ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ተናግረው፤ "ከዚህ ቀደም ይደርስ የነበረው አይነት ጉዳትን እያደረሰ ይገኛል" ብለዋል።

14 ወራትን ያስቆጠረው የትግራዩ ጦርነት እየተባባሰ ሄዶ በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሎ ነበር።

ከአንድ ወር በፊት የፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ማካሄዳቸውን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ይዘዋቸው የነበሩትን የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎችን ለቀው ወደ ትግራይ ተመልሰው እንደነበረ ይታወሳል።

ባለፉት ሳምንታት የፌደራሉ መንግሥት ሲያካሂዳቸው ከቆዩት የአየር ጥቃቶች ውጪ፤ ይህ ነው የሚባል የተጠናከረ ጦርነት ስለመካሄዱ ሳይዘገብ ቆይቷል።

ባለፉት ቀናት ግን የህወሓት ኃይሎች በከባድ መሳሪያ በመደገፍ በአዋሳኙ የአፋር ክልል ወረዳዎች ላይ ፈጽመውታል በተባለው ጥቃት በበርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የአፋር ክልል ገልጿል።

የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ቀደም ሲል በነበረው ጦርነት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተሰራ በነበረበት ወቅት አዲስ ጥቃት መከፈቱን ይናገራሉ።

በአዲሱ ጥቃት "ማኅበረሱ በተለያየ አቅጣጫ ተብትኖ ነው ያለው። ምን ያክል ሰው ተፈናቀል የሚለውን ማወቅ አይቻልም። ሕዝቡን ወደ አንድ ቦታ ለመሰብሰብ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል አቶ አሕመድ ለቢቢሲ ሲናገሩ።

'የፌደራሉ መንግሥት እርምጃ ይውሰድ'

የትግራይ ኃይሎች ሦስቱን አዋሳኝ ወረዳዎችን ሲቆጣጠሩ በስፍራው የፌደራል የመከላከያ ኃይል እንዳልነበረ አቶ አሕመድ ይናገራሉ።

"ክልሉ ላይ ወረራ እየተፈጸመ ነው። በአገር ሕልውና ላይ አደጋ ተጋርጧል። የንጹሃንን ሕልውና መጠበቅ አለበት። ስለዚህ የፌደራል መንግሥቱ አስፈላጊ እርምጃ መውስድ አለበት" ብለዋል።

አቶ አሕመድ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ዋና ተልዕኮ "የክልል ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው" ካሉ በኋላ፤ "በንጹሃን ላይ ጥቃት ሲፈጸም ልዩ ኃይሉ እጁን አጥጥፎ አይቀመጥም" ሲሉ ተናግረዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት

አብአላ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችለው ዋነኛው መንገድ የሚገኝባት የአፋር ክልል የወረዳ ከተማ ሰትሆን በስፍራው ባለው ጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ችግር እንደገጠመው ሲገለጽ ቆይቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአፋር ክልል በኩል የጦርነቱን መባባስ ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ላይ የእርዳታ አቅርቦት መደናቀፉን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ " በአፋር ክልል ላይ አዲስ በተከፈተው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሳቢያ ወደ መቀለ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጭነው ይጓዙ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ለመመለስ መገደዳቸውን" ገልጸው ለጥቃቱ ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።

ህወሃት በበኩሉ በአፋር እና ትግራይ ድንበር ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት በሰብአዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው በመጥቀስ ለዚህም ኃላፊነቱ የፌደራል መንግሥት፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥትና አጋሮቹ ናቸው ሲል ወቅሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ "ከሠመራ-በአብአላ-መቀለ በሚወስደው መስመር በኩል ወደ ትግራይ የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አብአላ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ማክሰኞ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ ይገኛል" ብሎ ነበር።

የፌደራሉ መንግሥት ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በየበስ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ፤ እንደ መድኃኒት እና ምግብ ያሉ መሠረታዊ የእርዳታ አቅርቦቶችን ለማድረስ ዕለታዊ በረራዎችን እንዲቀላጠፉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ከወራት በፊት ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን በተከታታይ ከተካሄዱ ከባድ ውጊያዎች በኋላ ከክልሎቹ መውጣታቸው ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከአንድ ወር በፊት ጋብ ያለ ቢሆንም ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የአፋርና የአማራ ክልሎች ውስጥ ውጥረትና ግጭቶች ሲካሄዱ መቆያታቸውን ሲዘገብ ነበር።

የተለያዩ ወገኖች በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መሪዎች መካከል ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ውይይት እንዲጀመር ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን በተጨባጭ የታየ ውጤት የለም።