በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ኬንያና አሜሪካ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ

ፕሬዝዳንት ኬንያታ ከአምባሳደር ሳተርፊልድ ጋር

የፎቶው ባለመብት, State house-keneya

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኬንያታ ከአምባሳደር ሳተርፊልድ ጋር

የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአካባቢው ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ኬንያና አሜሪካ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉ መስማማታቸው ተነገረ።

ይህ የተገለጸው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ናይሮቢ ውስጥ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በተወያዩበት ወቅት መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

አምባሳደር ሳተርፊልድ ፕሬዝዳንት ኬንያታ ግጭቱ እንዲያበቃ ያደረጉትን ጥረት በማድነቅ ሚናቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው ጥረታቸውም እንዲሳካ የአሜሪካ ድጋፍ እንማይለያቸው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ኬንያታም ኢትዮጵያና ኬንያ በተለይ በቴሌኮሚዩኒኬሽንና በመሰረተ ልማት ግንባታ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የተገኘውን ውጤት እንዳይጎዳ እንዲቆም መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ ጠንካራ መሆን ለእኛ ጠቃሚ ነው። የተረጋጋች ኢትዮጵያ ለእኛ ትጠቅመናለች። ለዚህም ነው ግጭቱ መፍትሔ እንዲያገኝ የምንችለውን ሁሉ የምናደርገው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የመጡት ባለፈው ሳምንት ሲሆን በዚህ ጉዟቸው ሱዳን እና ኢትዮጵያን ጎብኝተው የአገራቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማነጋገራቸው ተገልጿል።

የቀድሞውን ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን ተክተው ሥራቸውን የጀመሩት ሳተርፊልድ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ የሆኑት አምባሳደር ሞሊ ፊ ጋር ነው ጉብኝታቸውን የጀመሩት።

በዚህ ጉብኝታቸው በቀዳሚነት ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን በተመለከተ ወዳጆቿ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ነበር።

በተከታይነትም ወደ ካርቱም አምርተው ከአገሪቱ ወታደራዊ መሪዎችና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ውይይት አድርገው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከአፍሪካ ሕብረት ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፖሎማቶቹ ከዋሽንግተን ከመነሳታቸው በፊት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል ተገልጾ የነበረው ጉብኝቱ በሳዑዲ፣ በሴዳንና በኢትዮጵያ የሚካሄድ እንደነበረ የተገለጸ ቢሆንም አምባሳደሮቹ ኬንያ ተገኝተው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተወያይተዋል።

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙት የተቀዛቀዘው አሜሪካ ከኬንያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራለች።

የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ኬንያም ጦርነቱ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ስታደርግ የቆየች ሲሆን ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።