በአሜሪካ ፖሊስ በነጭ ተጠርጣሪ ሰበብ ጥቁር አሜሪካዊን በማሰሩ አነጋጋሪ ሆነ

ሼን ሊ ብራዎን (ግራ) እና ሼን ኒል ብራዎን

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, ሼን ሊ ብራዎን (ግራ) እና ሼን ኒል ብራዎን

በአሜሪካዋ ኔቫዳ ግዛት ፖሊስ ከነጭ ተጠርጣሪ ጋር ተመሳስሎበት አንድ ጥቁር አሜሪካዊን ለስድስት ቀናት አስሮ ማቆየቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

በፖሊስ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበት ሲፈልገው የነበረው ነጩ ግለሰብ ከጥቁር አሜሪካዊው በእድሜ በእጥፍ እንደሚበልጥ ጭምር ተገልጿል።

የ25 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ሼን ሊ ብራውን እአአ 2020 ላይ የመንጃ ፍቃዱን ማሳየት ባለመቻሉ በፖሊስ ተይዞ ነበር። ፖሊስ በወቅቱ በጥቁር አሜሪካዊው ስም የወጣ የእስር ማዘዣ ማግኘቱ ተነግሯል።

ይሁን እንጂ ይህ የእስር ትዕዛዝ የወጣው ሼን ኒል ብራውን የተባለን ግለሰብ ለመያዝ ነበር።

ሼን ኒል ብራውን ነጭ፣ ቡኒ ጸጉር እና ሰማያዊ አይን ያለው እንዲሁም ጺማም የ51 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ሳ፣ ፖሊስ የ25 ዓመቱን ወጣት ጥቁር አሜሪካዊ ከነጩ ጎልማሳ ጋር እንዴት ሊመሳሰልበት ቻለ የሚለው ጥያቄን አስከትሏል።

በስህተት ለቀናት ለእስር የተዳረገው ወጣት ጥቁር አሜሪካዊ ካሳ እንዲከፈለው አቤቱታ አቅርቧል።

ወጣቱ በእስር ላይ ሳለ በተደጋጋሚ በስም ላልተጠቀሱ የፖሊስ አባላት እና ኃላፊዎች የእስር ትዕዛዝ የወጣበት "ነጩ ሸን ብራውን" አለመሆኑን ተናግሯል ይላል በጥቁር አሜሪካዊው ላይ የተከፈተው የክስ መዝገብ።

በክስ መዝገቡ ላይ ፖሊስ በወንጀል የሚፈለገውን ነጭ አዛውን ፎቶግራፍን ከወጣቱ ጋር ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ አላነጻጸረም የሚል አቤቱታ ሰፍሯል።

የሄንደርሰን ከተማ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ፤ ወጣቱ የታገደ መንጃ ፍቃድ ይዞ ሲነዳ በመያዙ እስሩ ሕጋዊ ነበር በማለት ወጣቱ በነጩ ተጠርጣሪ ፈንታ በስህተት ስለመታሰሩ አስተያየት ሳይሰጡ አልፈዋል።

ሼን ሊ ብራውን ለአንድ ሳምንት ያህል ታስሮ ከቆየ በኋላ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ዳኛ የሁለቱን ግሰለቦች ፎቶግራፍ አነጻጽረው በመመልከት ወጣቱ ከእስር ወጥቷል።

አሁን ላይ ሼን ሊ ብራውን በፖሊስ በደረሰበት እንግልትና አስር ምክንያት የ500 ሺህ ዶላር ካሳ ጠይቋል።

ወጣቱ ከእስር ከተለቀቀ ከስምንት ቀናት በኋላ የላስ ቬጋስ ፖሊስ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበት የነበረው ሼን ሊ ብራውን ካሊፎርኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተገንዝቧል።