የአፋር ክልል ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መቀስቀሱ ተነገረ

የህወሓት ኃይሎች የአፋር ክልል ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ጥቃት መክፈታቸውንና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአፋር ክልል ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የህወሓት ኃይሎች በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል ጥሰው በመግባት በአብዓላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት ከፍተዋል ብሏል።
ህወሃት በበኩሉ የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታን ለማደናቀፍ በአፋር በኩል ያለውን ጦርነት እየተጠቀመበት ነው በማለት በትናንትናው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።
የኤርትራና የአፋር ክልል ሃይሎች በአፋርና ትግራይ ድንበር በአብዓላ በኩል ጦርነት እንደከፈቱና ይህም ሆን ተብሎ የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎችን ለማገድ ጦርነት እንደ ሰበብ ለመጠቀም እንዲያስችለው ነው ሲል የፌደራል መንግሥቱን ከሷል።
ባለፉት ሳምንታት የአፋር ክልልን ከትግራይ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በህወሓት ኃይሎች እየተፈጸመ መሆኑን የአፋር ክልል ሲገልጽ የቆየ ሲሆን ከትግራይ በኩልም እንዲሁ የአፋር ልዩ ኃይል ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ ሲቀርብ ነበረ።
የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በአማርኛ ወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት መክፈታቸውን የገለጸ ሲሆን በእንግሊዝኛ ባወጣው መግለጫ ላይ ደግሞ አማጺያኑ ዘልቀው በመግባት ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን አመልክቷል።
መግለጫው ሰኞ ዕለት የህወሓተው ታጣቂዎች "መጋሌ እና አብአላን የተቆጣጠሩ ሲሆን በበራህሌ በኩል አሰዳ አካባቢ ከባድ ውጊያ መቀስቀሱን" ገልጿል።
ጦርነቱ በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ በመሆኑ በአካባቢው በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰም ጨምሮ የገለጸ ሲሆን በርካታ ሰዎች ከጥቃቱ ለመሸሽ አካባቢያወቸውን ለቀው ወደ አቅራቢያ ቦታዎች እየሄዱ መሆኑ ተነግሯል።
አብአላ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችለው ዋነኛው መንገድ የሚያልፍበት በአፋር ክልል የሚገኝ ስፍራ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የአቅርቦት ችግር እንደተከሰተ ሲገልጽ ቆይቷል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአፋር ክልል በኩል የጦርነቱን መባባስ ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ላይ የእርዳታ አቅርቦት መደናቀፉን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ " በአፋር ክልል ላይ አዲስ በተከፈተው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሳቢያ ወደ መቀለ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጭነው ይጓዙ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ለመመለስ መገደዳቸውን" ገልጸው ለጥቃቱ ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ህወሃት በበኩሉ በአፋር እና ትግራይ ድንበር ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት በሰብአዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው በመጥቀስ ለዚህም ኃላፊነቱ የፌደራል መንግሥት፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥትና አጋሮቹ ናቸው ሲል ወቅሷል።
የአፋር ክልል መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች በኩል ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተበተ፣ አንዳንድ ቦታዎች እንደተያዙና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በተመለከተ ላወጣው መግለጫ ከህወሓት በኩል ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ ዕለት ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "በአብዓላ በኩል የተከሰተው ጦርነት በአፋር ኃይሎች እና በኤርትራ አጋሮቻቸው አማካይነት የተቀሰቀሰ ነው" ብለዋል።
ከወራት በፊት ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማረና አፋር ክልሎች በመግባት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን በተከታታይ ከተካሄዱ ከባድ ውጊያዎች በኋላ ከክልሎቹ መውጣታቸው ይታወሳል።
አሁን ከባድ ውጊያ እየተደረገባቸው ያሉት የአፋር ክልል አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል በየብስ በትራንስፖርት የተለያዩ የእርዳታ አቅርቦት የሚደርስበት ብቸኛው መንገድ ነው። አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት የእርዳታ አቅርቦቱ ላይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከአንድ ወር በፊት ጋብ ያለ ቢሆንም ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የአፋርና የአማራ ክልሎች ውስጥ ውጥረትና ግጭቶች ሲካሄዱ መቆያታቸውን ሲዘገብ ነበር።
የተለያዩ ወገኖች በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መሪዎች መካከል ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ውይይት እንዲጀመር ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን በተጨባጭ የታየ ውጤት የለም።












