የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ያቀረበውን አቤቱታ ሳይመለከት ቀረ

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት በዳይሬክተሩ ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ እንዲከፈትባቸው ያቀረበውን ጥያቄ ሳይመለከተው ቀረ።

ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው ሰኞ ጥር 16/2014 ዓ.ም በጄኔቫ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ በኃላፊው ገለልተኝነት ላይ ያቀረበችውን የይመርመሩልኝ ጥያቄም በአሁኑ ወቅት ላለማየት እንደወሰነ መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

ዶክተር ቴድሮስ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ዕጩ በሆኑበት ጉዳይ ላይ ለመወያየት በተጠራ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ጥያቄ ወደ ጎን መገፋቱን የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ፓትሪክ አሞት ተናግረዋል።

"ይህ ጉዳይ በጣም የተወሳሰበና ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ከዚህ ኮሚቴ የአስራር ማዕቀፍ ውጪ ነው" ያሉት አሞት "በዚህም መሰረት ይህ ጥያቄ ወደ ጎን እንዲገፋና ተገቢም ሆኖ ከተገኘ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል ወደሚለው ሃሳብ አዘነብላለሁ" ብለዋል።

የቦርዱ 34 አባላት በሙሉ ያልተቃወሙት መሆኑን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን ነገር ግን በጄኔቫ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ቆርቾ በኋላ ላይ በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር ዶክተር ቴድሮስን በመተቸት ንግግር ሊያቀርቡ ቢሞክሩም ሁለት ጊዜ መከልከላቸውንና በመጨረሻም እንዲቆረጡ መደረጉም ዘገባው አስነብቧል።

"በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት አግባብነት የሌለውና ሕግና አሰራሩንም ያልተከተለ ነው በማለት" ፓትሪክ አሞት አስረድተዋል።።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ውሳኔው የዓለም ጤና ድርጅት በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ አለመሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት በቴድሮስ ላይ ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ይጠይቃልም ሲሉ ለሮይተርስ በጻፉት መልዕክት ቃለ አቀባዩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የድርጅቱን ነፃነት፣ ገለልተኝነት መርህ ጥያቄ ውስጥ እንደከተቱት በመጠየቅ ምርመራ እንዲከፈትባቸው ጠይቆ ነበር።

ኢትዮጵያ ዶክተር ቴድሮስ የሥነ ምግባር፣ የሙያ እና ሕጋዊ ጥሰቶችን በመፈጸምና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣትም ተጠያቂ እንደሆኑ ለድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ቦርድ በላከችው የቅሬታ ማመልከቻ ላይ አስገብታለች።

ዶክተር ቴድሮስ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ እንደሚከለክል የሚናገሩ ሲሆን በቅርቡም በትግራይ ያለውን ሁኔታ ከሲኦል ጋር አወዳድረውታል።

የድርጅታቸው እንቅስቃሴዎች የከፉ ጦርነቶች ባሉባቸው እንደነ ሶሪያና የመን እንኳ ባልተገታበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ባልታየ ሁኔታ እግድ እንደሚጣልባቸው አውስተዋል።

"በትግራይ የመድኃኒት እጦት ሰዎች በየቀኑ እንዲሞቱ እያደረገ ነው። የምግብ እጦትም በየቀኑ ሰው ይገድላል። ይህ ሁሉ ሳያንስ በየቀኑ የድሮን ጥቃት መፈጸምና ዜጎች በፍርሃት ተሰቅዘው እንዲቆዩ ማድረግ ትክክል አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር እና የጤና ሚንስትር ሆነው ለረዥም ዓመታት ማገልገላቸው ይታወሳል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ከታኅሣሥ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ አልገቡም።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን ከአምስት ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ለመድረስ ከታሰበ በየሳምንቱ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ክልሉ ሊገቡ ይገባል ቢልም፣ እንደ ኦቻ ሪፖርት ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ከሚያስፈልገው አቅርቦት ውስጥ 12 በመቶ ብቻ ነው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።