በትግራይ ምግብ ከሚለምኑት መካከል ዶክተሮች ይገኙበታል

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል ያሉ አንዳንድ ዶክተሮች እና ነርሶች ራሳቸውን ለመመገብ ምግብ እየለመኑ መሆኑን አንድ የህክምና ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለስምንት ወራት ያህል ደመወዝ ሳይከፈላቸው በመቆየቱም ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ሌሎች አማራጭ መንገዶች እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል ይላሉ።
ዶክተሩ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርትም የከፋ ረሃብ በትግራይ ማጋጠሙን አስታውቋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው 2.2 ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪዎች "በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው" ይላል የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት።
ክልሉ ውስጥ ባለው ቀውስም ዶክተሮች እና ነርሶች ከስቃዩ አልዳኑም።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በትግራይ መዲና መቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል ዶክተር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ነርሶች እና ዶክተሮች ምግብ ለመቀበል ሲሰለፉ ማየት የተለመደ ሆኗል።
በምግብ እጦት የሞተው ህፃን
የህክምና ባለሙያዎቹ ካለፈው ዓመት ግንቦት ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈላቸውም።
"አብዛኞቹ በቀን የሚበሉትን ቁጥር ቀንሰዋል። የምግብ ዘይት፣ አትክልት፣ እህል ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ በመናሩ መግዛት የማይታሰብ ነገር ነው። አንዳንዶች ምግብ መለመን ጀምረዋል" ብለዋል ዶክተሩ።
የህክምና አቅርቦቶች እጥረት የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት እንዴት እንደጎዳው ያስረዳሉ።
አይደር ሆስፒታል በቀዶ ህክምና ወቅት እና ከቀዶ ህክምና በኋላ ቁስል ለማፅዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው ፋሻ በመጠቀም ፋንታ ከልገሳ የሚገኙ የተቆራረጡ ልብሶችን በፀረ ተህዋስያን እያጸዱ መጠቀም ግዴታ ሆኖባቸዋል።
በቅርቡ በከፍተኛ ምግብ እጥረት ይሰቃይ የነበረው የሦስት ወሩ ህፃን ሱራፌል ማዕረግ በተመለከተ ቢቢሲ በቅርቡ ዘግቦ የነበረ ሲሆን ህፃኑም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ዶክተሩ ተናግረዋል።
ጨቅላው ህክምና ካደረገ በኋላ ክብደቱ ትንሽ እየጨመረ ስለመጣ ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ቤት ቢላክም ቤት ውስጥ ምንም አይነት ምግብ ባለመኖሩ ጥር 05/2014 ዓ.ም አርፏል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ስለሌለው ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ዝርዝሩን ማረጋገጥ አልቻለም።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች መቋረጣቸው ወሳኝ እርዳታ እና የህክምና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ፈታኝ አድርጎታል።
የባንክ አገልግሎትም በመቋረጡም ምክንያት የክልሉ ነዋሪዎች ገንዘብ ማግኘት ተስኗቸዋል፣ እንዲሁም ሌሎችንም ለመክፈል አልተቻለም።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው ከጠቅላላው ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች መካከል ግማሽ ያህሉ በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።
በአጠቃላይ በትግራይ እና ጦርነቱ በተከሰተባቸው አጎራባቾቹ የአማራ እና አፋር ክልሎች ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
ሆኖም ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የህክምና እርዳታ ወደ መቀለ ማስገባቱ በዚህ ሳምንት ሳምንት መጠነኛ እፎይታ ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁሟል።
ከታኅሣሥ ጀምሮ ምንም አይነት የምግብ እርዳታ መግባት እንዳልቻለ ተመድ ቢያስታውቅም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን ረሃብ ለመከላከል 100 የጭነት መኪኖች በቀን ያስፈልጋሉ ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለሚደረገው እርዳታ 337 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እየጠየቀ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
ባለፉት ወራት የፌደራሉ ጦር የትግራይ ኃይሎችን ግስጋሴ ቢገታም በምዕራብ ትግራይ፣ በአማራና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በአፋር ክልል፣ በሰሜን ጎንደር በዋግ ኸምራና በሰሜን ወሎ ዞኖች በትግራይ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ውጊያው ቀጥሏል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሰላም ለማውረድ ድርድር ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋም ታይቷል።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን የአፍሪካ ህሕረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆም ከፍተኛ የትግራይ መሪዎችን አነጋግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቧል።












