በትግራይና በተለያዩ አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች መኖራቸውን ተመድ አስታወቀ

የአፋር ልዩ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የምስሉ መግለጫ, የአፋር ልዩ ኃይል አባላት

በትግራይና በተለያዩ አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች መኖራቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እና ሊተነበይ የማይችል አድርጎታል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ገለጸ።

ውጊያዎች በምዕራብ ትግራይ፣ በአማራና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በአፋር ክልል፣ በሰሜን ጎንደር በዋግ ኸምራና በሰሜን ወሎ ዞኖች ሪፖርት መደረጉን ኦቻ ጥር 20/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ኦቻ እንዳለው በተጨማሪም በትግራይ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሽራሮ ከተማ፣ በወልቃይት ፀገዴ እንዲሁም በምዕራብ ዞን ሁመራ አካባቢዎች ውጊያው ቀጥሏል።

በአፋር ክልልም መጋሌ፣ ኢሬብቲ፣ በራህሌ፣ ዳሎል እና አብዓላ ጦርነት መኖሩ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።

ከቀናት በፊት የህወሓት ኃይሎች ከትግራይ ክልል አዋሳኝ የሆኑ በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

የህወሓት ኃይሎች ደግሞ ከአፋር ኃይሎች በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰኞ ጥር 16/2014 'ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ መገደዳቸውን" ገልጸዋል።

በአፋር ክልል ያለው ጦርነት በህወሓትም ሆነ በአፋር ክልል በኩል እውቅና ተሰጥቶት የተነገረ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ውጊያዎችን በተመለከተ ከፌደራሉ መንግሥት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

የቀጠሉት ግጭቶች የዜጎችን ህይወት ለበለጠ ለአደጋ እያጋለጡ እንደሆነ የጠቆመው የኦቻ መግለጫ ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስም እንቅፋት እንደፈጠረ አፅንኦት ሰጥቷል።

በትግራይ ክልል በሰመራ- አብዓላ-መቀለ ኮሪደር እንዲሁም በአፋር እና በአማራ ክልሎች ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ ማድረስ አልተቻለም።

በአፋር በተደረገው ጦርነት ባለፉት ሳምንታት ብቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል ብሏል ሪፖርቱ።

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በኡሩክዲ፣ ጉቤ፣ በዞን 2 ኢሬቢቲ እና አፍዴራ ከተማ በሚገኙ ሦስት የመጠለያ ጣቢያዎችም ላይ ገብተዋል።

ቀደም ሲል የነበሩት ተፈናቃዮች ጉዳይ እልባት ሳያገኝ አዲስ የመፈናቀሉ ጉዳይ መከሰቱ ቀድሞውንም አስቸጋሪ በሆነው ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን አጣብቂኝ ውስጥ እያስገባው መሆኑንም የኦቻ ሪፖርት ጠቅሷል።

በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የተደረጉ ውጊያዎችን ተከትሎ ከአፋር እና አማራ ክልሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ ተፈናቃዮች ወደ ውቅሮ አፅቢና አጉላዕ ወረዳዎች ደርሰዋል፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደርም እንዲሁ የተፈናቃይ ዜጎች ሪፖርቶች ለኦቻ ደርሷል።

ለአዲሶቹ ተፈናቃዮችም ምግብ፣ የድንገተኛ አደጋ መጠለያ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች፣ ውሃ እና የንፅህና መጠበቂያዎች እና የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት አስፈላጊ መሆናቸውንም አስምሯል።

በሳምንቱም ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መጡበት መመለሳቸው ሪፖርት መደረጉን ቀጥሏል።

በአፋር ክልል በዋክ/50 እና በኢዋ መጠለያ ካምፖች የነበሩ 30 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ጭፍራ እና ኢዋ ወረዳዎች መመለሳቸው ተነግሯል።

አብዛኞቹ በፍቃደኝነት የተመለሱ ቢሆንም፣ የተወሰኑት ያለፈቃዳቸው እና ተገቢውን የኑሮ ድጋፍ ሳያገኙ መመለሳቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የወደሙ፣ የተበላሹ እና የተዘረፉ እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና የውሃ አገልግሎቶች የመሳሰሉት የሕዝብ መሰረተ ልማቶች ሳይስተካከሉ መመለስ ምቹ እንዳልሆነም ኦቻ ያስረዳል።

በትግራይ ከ8,800 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ምሥራቅ፣ መካከለኛው፣ ደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ዞኖች ባሉ የመኖሪያ ስፍራዎቻቸው ከታኅሣሥ መጀመሪያ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ መመለሳቸውን ሪፖርቱ ያትታል።

በተጨማሪም በሰሜን ምዕራብ ዞን ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ወደ አዲ ሃገራይ ወረዳ መመለሳቸው ተነግሯል።

በአጠቃላይ በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ሁኔታ የገመገመው ሪፖርቱ በአፋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከታኅሣሥ መጀመሪያ ጀምሮ በሰመራ-አብአላ-መቀሌ ኮሪደር በኩል ምንም አይነት የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ መድረስ አልቻለም።

ከሐምሌ መጀመሪያ ጀምሮ 1 ሺህ 338 የእርዳታ ጭነት መኪናዎች ወደ ክልሉ የገቡ ሲሆን ይህም እርዳታ ከሚያስፈልገው 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ 10 በመቶ በታች የሚሆነውን ብቻ ነው መድረስ የተቻለው።

በክልሉ ያለው የምግብ አቅርቦት እየተመናመነ መሆኑን ያስተወቀው ኦቻ አጋሮች ያላቸው ድርጅቶች ከሦስት ቀናት በፊት የነበራቸው የምግብ ክምችት 1 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ይህም 20 ሺህ ሰዎችን በአንድ ዙር የሚመግብ ነው ብሏል።

በተመጣጠነ ምግብ ችግር የሚሰቃዩ ሰዎችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ አልሚ ምግቦች ክምችት ማለቁንም አስታውቋል።

ክልሉ በነዳጅ እጥረትም ከፍተኛ ችግር ያጋጠመው ሲሆን በሰመራ ከተማም ከ155 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ የጫኑ መኪኖች አሁንም ፍቃድ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያስረዳል።

ከነሐሴ 22 ጀምሮም ከሁለት የዓለም ምግብ መኪኖች በስተቀር ምንም አይነት ነዳጅ ወደ ትግራይ እንዲገባ ፍቃድ አለመሰጠቱንም ከሪፖርቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የነዳጅ እጥረቱም የረድኤት ድርጅቶች የምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒትና ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎች ስርጭት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ገልጿል።

በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከአራት ቀናት በፊት እንዳሳወቁት የነዳጅ ክምችታቸው በመሟጠጡ ምክንያት ሰራተኞቻቸው እርዳታ ለማደረስ በእግር እየተጓዙ መሆናቸውን ነው።

በተመሳሳይ በትግራይ ለተቸገሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እየደረሱ ያሉት አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከባለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ ገንዘብ ማስገባት በነዳጅ እና በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ስጋት ላይ መሆናቸውን ነው።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቧል።