የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች በኃይል መቆራረጥ ክስ ተመሰረተባቸው

የኤሌክትሪክ መመስመር የሚጠግኑ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኬንያ ሃገር አቀፍ የኃይል መቆራረጥን ተከትሎ ሶስት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት ኃላፊዎች ክስ ተመሰረተባቸው።

ኃላፊዎቹ ሆን ብለው የኃይል መቆራረጥን አስከትለዋል እንዲሁም በቸልተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሌሎች የድርጅቱ ስድስት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈትተዋል።

ሃገር አቀፍ የኃይል መቆራረጡ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆይቷል ተብሏል።

ከሳምንት በፊት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን (ቮልቴጅ) መስመር መሰበሩን ተከትሎ አገሪቷ በድቅድድ ጨለማ ተውጣ ነበር። የኤሌክትሪክ ኃይሉም ከሰዓታት በኋላ በየደረጃው ተመልሷል።

በክሱ መሰረት ሶስቱ ኃላፊዎች ከፍተኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን ባለማስተካከላቸው እንዲሁም ሆን ብለው መብራት ከመቋረጡ ከሳምንታት በፊት የተበላሹትን ማማዎች ሳይጠግኑ ቸል በማለታቸው ተከሰዋል።

ሶስቱም ግለሰቦች ክሱን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን እያንዳንዳቸውም በ10 ሺህ ዶላር ዋስ ተለቀዋል።

የፍርድ ሂደታቸውም ለየካቲት መጨረሻ ተቀጥሯል።

ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የመሰረተ ልማት ውድመት በተለይም የመንግሥት ይዞታዎች ላይ መበራከቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ድርጊቱ ሆን ብሎ ምጣኔ ኃብቱን ለማቆርቆዝ የሚደረግ ደባ ነው በማለት ዘርፉን የሚቆጣጠር መመሪያ እስካልተዘጋጀ ድረስ በቁርጥራጭ ብረታ ብረት ላይ የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ሽያጭ ከልክለዋል።