"ዶክተር ነኝ፤ ከአምስት ዓመታት በላይ ገላዬን አልታጠብኩም" ለምን?

የፎቶው ባለመብት, James Hamblin
ዶ/ር ጄምስ ሐምብሊን ይባላል። 37 ዓመቱ ነው። በታላቁ የዬል ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር ነው። የበሽታ መከላከል ላይ ተጨማሪ የድኅረ ምረቃ ሕክምና ዲግሪ ጭኗል።
ይህ የተከበረ ሐኪም የሆነ ቀን፣ [ከአምስር ዓመት በፊት]፣ ድንገት ገላውን መታጠብ አቆመ።
"ትለምጅዋለሽ፣ ኖርማል ነው፤ ብዙም አይግረምሽ" ብሏታል ለቢቢሲዋ ጋዜጠኛ።
ዶ/ር ጄምስ ከዋና ሥራው በተጓዳኝ ለስመጥሩ የአሜሪካ አትላንቲክ መጽሔት አምደኛ ሆኖ ይሠራል። በ2016 የጻፈው ጽሑፍ ርዕስ "ገላዬን መታጠብ አቁሜያለሁ፣ እና ምን ይጠበስ?" የሚል ነበር።
ከርዕሱ ይልቅ የመጀመሪያው አንቀጽ ይበልጥ ያስገርማል።
"ዕድሜያችንን ሙሉ ገላችንን በመታጠብ ያባከንነው ገንዘብና ውሃ ሲያሳዝን? ለውሃም ጡር አለው" ይላል።
በአገሩ አቆጣጠር በ2020 ዓ.ም ደግሞ ደለብ ያለ መጽሐፍ ጽፎ አሳተመ።
መጽሐፍ ማሳተሙ አይደለም የሚገርመው። የመጽሐፉ ይዘት ነው ምጸቱ። "አዲሱ የቆዳ ንጽሕና አጠባበቅ" ይላል።
እሱ ራሱ ገላውን ሳይታጠብ ስለ ንጽሕና የሚያወሳ መጽሐፍ መጻፉ ሊያስገርም ይችላል። ነገሩ ይኸው ነው።
ምንም እንኳ ዶ/ር ጄምስ እጃችንን በሳሙና ደጋግመን መታጠብ፣ ጥርሳችንን በቀን 2 ጊዜ መቦረሽ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ቢያሳስብም፣ ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችንን ግን ቀን በቀን እየፈተግን ማሰቃየት የለብንም ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ጄምስ መጀመሪያ ገላ መታጠብን ያቆመው ለሙከራ ነበር። ኋላ ላይ ነው ነገሩን የገፋበት።
"አንድ ሰው ሻወር ባይወስድ ምን ሊደርስበት እንደሚችል ለማየት ፈለግኩ" ይላል።
"አልፎ አልፎ ብቻ ገላቸውን የሚታጠቡ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፤ ግን ራሴ ልሞክረው ፈለኩ።"
ዶ/ር ጄምስ በ2015 (እአአ) ገላውን መታጠብ ላይ እቀባ ካደረገ በኋላ ምን ተፈጠረ?
"የተረዳሁት ነገር ሰውነታችንን በየቀኑ ባንታጠበው ለተወሰኑ ቀናት የመቆሸሽ ስሜት ይሰማን ይሆናል እንጂ እየቆየ ሲሄድ ምንም ጠረን አይኖረንም። በራሱ ጊዜ ጠረኑ እየተወገደ ይመጣል" ይላል።
"ብዙ ሰዎች ፀጉራቸውን ለማጽዳት ሻምፑ ይጠቀማሉ። ከዚያ ደግሞ ኮንድሽነር ይጨምሩበታል። ይህ እሽክርክሪት ነው። እነዚህን ነገሮች መጠቀም ብናቆም እንዲያውም ፀጉር የበለጠ የተፈጥሮ መልኩን እንደጠበቀ ሊቆይ ይችላል" ይላል።
ዶ/ር ጄምስ እንደሚለው ይህ ያለመታጠብ ሂደት በአንድ ጊዜ መሆን የለበትም። ቀስ በቀስ የሚጀመር ሂደት እንደሆነ ያስረዳል።
እሱ ያደረገው እንዲያ ነበር። መጀመሪያ ሳሙና፣ ሻምፑና ዲዮደራንት መጠቀምን እየቀነሰ መጣ። ከዚያ ገላውን በቀን ሁለት ጊዜ ከመታጠብ፣ በቀን አንድ ጊዜ ወደመታጠብ፣ ከዚያም አልፎ በሳምንት ወደመታጠብ፣ ከዚያም ጨርሶውኑ አለመታጠብ ደረጃ ላይ ደረሰ።
"ሻወር መውሰድን መናፈቅ የጀመርኩበት ጊዜ ነበር። አልዋሻችሁም፣ ታጠብ ታጠብ የሚለኝ ስሜት አስቸግሮኝም ያውቃል" ይላል ዶ/ር ጀምስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የገላ ጠረን እና የባክቴሪያ ነገር
ይህ አሜሪካዊ ፕሮፌሰር እንደሚለው ገላችን ጠረን የሚፈጥረው በቆዳችን ላይ በሚገኙ ባክቴሪያዎች የተነሳ ነው። ባክቴሪያዎቹ የሚመገቡት ደግሞ ላባችንን እና ከሰውነታችን የሚመነጨውን የቆዳ የተፈጥሮ ቅባት ነው።
በየቀኑ ገላችንን ለማጽዳት ሳሙናዎችን ስንጠቀም ታዲያ የቆዳችን የተፈጥሮ ቅባት ይጎዳል፤ በዚህም ባክቴሪያዎች ይረበሻሉ።
በተከታታይ ገላችንን በታጠብን ቁጥር የተፈጥሮ ዑደትንና የቆዳ፣ የቅባት፣ የላብና የባክቴሪያ ተፈጥሯዊ መስተጋብሩን [ኢኮሲስተሙን] እናዛባለን።
ቶሎ ቶሎ በታጠብን ቁጥር ቶሎ ቶሎ ባክቴሪያዎች መዋለድ ይጀምራሉ። ይህ ሁኔታ ጠረን የሚፈጥሩትን ደቂቃን [ማይክሮብስ] ምርት ይጨምርና ከበድ ያለ ጠረን ቶሎ ቶሎ እንዲከሰት ያደርጋል።
እዚህ ጋ አንድ ሰው ከቶውንም መታጠብ ሲያቆም ግን ይህንን ሂደት ስለሚሰብረው ሰውነቱም መጥፎ ጠረን ማውጣት ያቆማል።
"አለመታጠብ ሽቶ ሽቶ እንድንሸት አያደርገንም። አለመታጠብ እንድንከረፋም አያደርገንም። በቃ ሰው ሰው እንሸታለን፤ ተፈጥሯችንን" ይላል ዶ/ር ጄምስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ጄምስ ራሱ ምን ምን ይሸታል?
ለአምስት ዓመታት ገላዬን ውሃ ንክች አላደረገውም የሚለው ዶ/ር ጄምስ ገላው ይሸት ይሆን?
በነሐሴ 2020 የቢቢሲ የሳይንስ ጉዳዮች ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ነበር። አንድ ጥያቄ ተጠየቀ።
"እንደው ሐቁን እንነጋገርና ሰዎችን በመጥፎ ጠረኔ እያጠንኳቸው ይሆን እያልክ አትሰጋምን? ምናልባት ትሁት ሆነው ይሆን 'ትሸታለህ' ብለው ያልነገሩህ" ተባለ።
ሲመልስም "ሁሉንም ጓደኞቼን፣ የሚቀርቡኝን የማምናቸውን ሰዎች ሁሉ እውነቱን እንዲነግሩኝ ጠይቂያለሁ። ማንም 'መጥፎ ጠረን ታወጣለህ' አላለኝም።"
ዶ/ር ጄምስ በዚህን ጊዜ ነበር ባለመታጠብ ጠረን ሊወደግ እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር የጀመረው።
ዶ/ር ጄምስ ሌላም አስገራሚ ምላሽ ሰጥቷል።
"እውነት ለመናገር አዲሱ ጠረኔን ባለቤቴ እጅግ ወዳዋለች፤ ሌሎች ሰዎችም መጥፎ እንዳልሆነ ነግረውኛል" ይላል።
የዶ/ር ጄምስ በቆዳ ጤና አጠባበቅ ዙርያ የጻፈው መጽሐፍ እንዲሁ ለዋዛ የተጻፈ አይደለም። ዶ/ር ጄምስ አሁን ገበያ ላይ ያሉት የቆዳ ጤና መጠበቂያዎችና የንጽሕና መጠበቂያ ኢንዱስትሪው ጉዳይ ያሳስቡታል።
"ሳይንስን ከገበያ መለየት ይኖርብናል" ይላል፤ የገበያ ማስታወቂያ ጋጋታ ሳይንስን እየጋረደው እንደሆነ የሚሰማው ዶ/ር ጄምስ።
ብዙ ሰዎች በገበያ ማስታወቂያ ተገፋፍተው የሳሙናና የሻምፑ መሞከርያ እየሆኑ ነው፤ የምንጠቀመው ሳይንሱን አውቀን ሳይሆን ገበያው ገፍቶን ነው ብሎ ያምናል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ እያመዘነ መሆኑ ይሰማዋል።

የፎቶው ባለመብት, Luis Diaz Devesa
ዶ/ር ጀምስ ታሪካዊ ዳራ በመስጠት ሙግቱን ይቀጥላል
"ከመቶ ዓመት በፊት ብዙ ሰዎች የቧንቧ ውሃ አልነበራቸውም። ወንዝ ወርዶ መታጠብ የነበረ ቢሆንም ይህ በየቀኑ የሚደረግ ነገር አልነበረም። ያን ጊዜ አንድን ነገር በብዙ ቁጥር ማምረት አልተጀመረም ነበር።
"ያን ጊዜ በጀምላ የሚመረቱ ሳሙናዎች አልነበሩም፤ በተፈጥሮ ያገኘነውን ስንጠቀም ነው የኖርነው። በዚያ ወቅት አሁን ያለው ውስብስብ የቆዳ ችግር አልነበረም። ስለዚህ ምናልባት ችግሩ ከምንጠቀማቸው ምርቶች ሳይሆን አይቀርም።
"በቆዳችን ላይ ያለው ባክቴሪያ በአንጀታችን ላይ እንደሚገኘው ባክቴሪያ ለሰውነት በጣም አስፈላጊ ባክቴሪያ ነው። ነገር ግን እነዚህ ባክቴሪያዎች መጥፎ ነገር እንደሆኑ ተደርገው ተሰብከናል። ሀቁ በተቃራኒው ነው፤ ብዙዎቹ ባክቴሪያዎች በሽታን አምጪ አይደሉም። መወገድም የለባቸውም" ይላል ዶ/ር ጀምስ።
ገላን መታጠብ ያለው ፋይዳ በዘመነው ዘመን ተጋኖ ይሆን?
ንጹህ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚያግባባ ድምዳሜ ላይ አልደረስንም። ስለዚህ ነው ገላን መታጠብ የተጋነነ ትርጉም የተሰጠው።
"እንደኔ እንደኔ የሰዎች ምርጫ ነው እንጂ በየቀኑ ገላን መፈተግ በሕክምና የሚደገፍ ተግባር አይደለም" ይላል።
ዶ/ር ጄምስ ሲያክል፣ "እኔ ሰዎች ገላችሁን መታጠብ አቁሙ እያልኩ አይደለም፤ ነገር ግን በተለይ የቆዳ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ቀስ በቀስ አዘውትሮ አለመታጠብን ቢሞክሩት ውጤት ሊያገኙበት ይችላሉ" ይላል።
ከሻምፑውም ከዶድራንቱም ቀነስ እያደረግን እንሞክረው ሲል ይመክራል።
"ገበያ ገበያ ከምንሸት፤ ሰው ሰው መሽተተ ብንጀምር እላለሁ" ይላል ዶ/ር ጀምስ።
ምክሩን እንሞክረው ይሆን?. . .

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












