የጋዳፊን ልጅ ጉዳይ በሚመለከተው ፍርድ ቤት ላይ የደረሰው ጥቃት አሳስቦኛል - ተመድ

ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ የሊቢያ መሪ ልጅ ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ይግባኝ ባቀረበበት ፍርድ ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳስቦኛል አለ።

ሰይፍ አል-ኢስላም በሊቢያ ለሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፍ መከልከሉን ተከትሎ ጠበቃው ይግባኝ ባሉበት ፍርድ ቤት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉዳዩ እንዳሳሰበው የገለጸው።

የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ ጋዳፊ ከሳምንታት በኋላ በአገሪቱ ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር ውጪ የተገደረገው ሐሙስ ዕለት ነበር።

የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊን እአአ 2015 ከቀረቡበት የጦር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ነበር ከምርጫ ተሳታፊነቱ ያገደው።

ኮሚሽኑ ከጋዳፊ ልጅ በተጨማሪ በርካታ ዕጩዎችን "በሕጋዊ ምክንያቶች" በምርጫው እንዳይሳተፉ ማገዱን አሳውቋል።

አል ኢስላም ጋዳፊ አባቱ የሰሜን አፍሪካዊት አገር ሊቢያን በሚያስተዳደሩበት ወቅት በተፈጸሙ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል እና በነፍስ ግድያ የሚፈለግ ሰው ነበር።

በዚህም ሳቢያ የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ከተሰማ በኋላ ውዝግብ አስነስቷል።

የሰይፍ አል-ኢስላም ጠበቃ ካህሊ አል-ዛኢዲ ሴባህ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት የደንበኛውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳያቀርብ የታጠቁ ሰዎች እንደከለከሉት ተናግሯል።

ሴባህ ከተማ ሊቢያን ለመቆጣጠር ነፍጥ ካነሱት አንዱ በሆኑት ጄነራል ኻሊፍ ሃፍጣር ቁጥጥር ሥር ትገኛለች።

በተመሳሳይ በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዝነኛው ኻሊፍ ሃፍጣር ለዚሁ ምርጫ ለመወዳደር መዘጋጃታቸው በአገሪቱ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሯል።

ነገር ግን ምርጫ ኮሚሽኑ ኻሊፍ ሃፍጣርን ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ውጪ ያድርጋቸው አይድርጋቸው የታወቀ ነገር የለም።

የሊቢያ ወታደራዊ ዐቃቤ ሕግ የጋዳፊ ልጅ እና የሃፍታር በቀረበባቸው ክስ ላይ ተገቢ መልስ እስኪያቀርቡ ድረስ የምርጫ ኮሚሽኑን በዕጩነት ለማሳተፍ የሚያደርገውን ሂደት እንዲያቆም ጠይቀው ነበር።

ሰኞ በተጠናቀቀው የዕጩዎች ምዝገባ ስልሳ ሰዎች ሊቢያን በፕሬዝዳንት ለመምራት የተመዘገቡ ሲሆን የ46 ዓመቷ የሴቶች መብት ተሟጋች ሊላ ቤን ካሊፋ ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ናቸው።