ሳይፍ ጋዳፊ - የቀድሞው የሊቢያ መሪ ልጅ 'ፕሬዝደንታችሁ አርጋችሁ ምረጡኝ' እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአማር አል-ጋዳፊ ልጅ በሚቀጥለው ወር በአገሪቱ በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ መመዝገቡ ተሰምቷል።
ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ በአንድ ወቅት ከአባቱ ሥልጣን ለመረከብ ጫፍ የደረሰ ሰው ነበር። ነገር ግን ከ10 ዓመት በፊት ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን በደል መደገፉ ስሙ እንዲጠለሽ አድርጎታል።
ከዚህ ተቃውሞ በኋላ ሊቢያ ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋቷ መመለስ ፈጽሙ አልቻለችም።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች በሚወጥለው ወር የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ኃያላን የሚባሉ አገራትና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሞክር አሊያም ውጤት የሚያዛባ አካል ከባድ እርምጃ ይወሰድበታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በይነ መረብ ላይ የተሰቀሉ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች፤ ሳይፍ ጋዳፊ ከአንድ የማስታወቂያ 'ፖስተር' ፊት ቆሞ በምርጫው ለመሳተፍ ሲመዘገብ አሳይተዋል።
ፊቱ በፂም የተወረረውና በሊቢያ ባሕላዊ ልብስ ያሸበረቀው ሳይፍ ከቁርዐን ላይ ምዕራፎችን እየመዘዘ ለከበቡት ካሜራዎች ተናግሯል።
ሳይፍ አሁን ያለው አቋምና አባቱ ጋዳፊ ሥልጣን ላይ እያሉ ያሳይ የነበረው አቋም ፍፁም የተለያዩ ሆነው ተስተውለዋል።
አባቱ በፈረንጆቹ 2011 ከሥልጣን ሲወገዱ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ በሚሊሻዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።
በሚሊሻዎች ቁጥጥር ስድስት ዓመታትን ካስቆጠረ በኋላ ሞት ተፈርዶበት ነገር ግን ይህ ፍርድ የኋላ ኋላ ሊቀለበስ ችሏል።
የጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አሁንም በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] በጦር ወንጀሎች ይፈለጋል።
ሳይፍ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው ቀስ በቀስ ሲሆን በተለይ ዚንታን ከሚገኘው ቪላ ቤቱ ሆኖ ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ያደረገው ቃል ምልልስ ብዙ ተመልካች አግኝቷል።
እንደ ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ባልደረባ አሚራ ፋታላ ዘገባ ከሆነ የጋዳፊ ልጅ በምርጫው ለመሳተፍ መመዝገብ ሊቢያዊያንን ለሁለት ከፍሏል።
ነገር ግን ለዓመታት አባቱን ይተካል እየተባለ ሲጠበቅ ስለነበር ወደ ሥልጣን ለመምጣት ማሰቡ ብዙም አስገራሚ አልሆነም።
ቢሆንም የቀጣዩን ወር ምርጫ ለማሸነፍ ቀላል እንደማይሆንለት የቢቢሲ መካከለኛው ምሥራቅ አርታኢ ሴባስቲያን አሸር ይናገራል።
አርታኢው ወትሮውንም በቋፍ ላይ የሚገኘው የሊቢያ ምርጫ በጋዳፊ ልጅ ወደፊት መምጣት ምክንያት እንዳይናወጥ ስጋት አለው።
ለዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየችው ሊቢያ አሁን በጊዜያዊ መንግሥት አስተዳደር ሥር ብትሆንም አሁንም አለመረጋጋት አለ።
በሊቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በምርጫው ሕግና ቀነ ቀጠሮ ምክንያት የተነሳው አለመግባባት ፕሬዝደንታዊውን ምርጫ እንዳያመክነው ስጋት ጭሯል።
በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገቡት መካከል የአገሪቱን ምሥራቃዊ ክፍል የተቆጣጠረውን አማፂ ቡድን ይመሩ የነበሩት ኻሊፋ ሐፍጣርና በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት የሚያስተዳድሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል-ድቤባህ ይገኙበታል።












