ለ25 ዓመታት በፖሊስ የተፈለገው የባንክ ዘራፊ ከሞተ በኋላ ማንነቱ ታወቀ

የፎቶው ባለመብት, US MARSHALS SERVICE
በአሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ሲፈለጉ ከነበሩ ባንክ ዘራፊዎች አንዱ የሆነው ግለሰብ ከ52 ዓመታት በኋላ ማንነቱ ታወቀ።
እአአ በ1969 የባንክ ሠራተኛ የነበረው ግለሰብ በወቅቱ ይሠራበት ከነበረው ባንክ 215,000 ዶላር ዘርፎ ተሰውሯል። ይህ ገንዘብ ዛሬ ባለው ተመን 1.7 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል።
ቴድ ኮናርድ የተባለው ዘራፊ ማንነቱ ሳይታወቅ ለ25 ዓመታት ቆይቷል።
ባንክ ከዘረፈ በኋላ "ድምጹን አጥፍቶ ሲኖር ነበር" ብለዋል የአሜሪካ የፀጥታ ኃይሎች።
ባንኩን ሲዘርፍ ገና የ20 ዓመት ወጣት የነበረው ቴድ፤ በቅርቡ በሳምባ ካንሰር ምክንያት ሕይወቱ አልፏል።
ይሠራበት ከነበረው ባንክ ገንዘቡን የሰረቀው አርብ ማታ ነበር። ገንዘቡን በፌስታል ከቶ ሳይታወቅበት ከባንኩ ከወጣ በኋላ ኑሮውን በድብቅ ሲመራ መቆየቱ ተነግሯል።
ሌሎች የባንኩ ሠራተኞች ገንዘብ መሰረቁን ያወቁት ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር።
ስለ ዝርፊያው ለፖሊስ ከጠቆሙ በኋላ ቴድ በእግር በፈረስ ቢፈለግም ለ25 ዓመታት ያህል ያለበት ሳይታወቅ ቆይቷል።
በአሜሪካ ታዋቂ በሆኑ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሮች ላይ "እጅግ ተፈላጊ ዘራፊ" በሚል ስለ ቴድ ተነግሯል።
ቴድ ባንክ ለመዝረፍ ቀላል እንደሆነና እሱም ባንክ የመዝረፍ እቅድ እንዳለው ለጓደኞቹ ሲናገር ነበር።
እአአ በ1968 የተሠራውን "ዘ ቶማስ ክራውን አፌር" የተባለውን የስቲቭ መክዊን የባንክ ዘረፋ ፊልምን እንደሚወደውም ተነግሯል።
ለባንክ ዘረፋው ሲዘጋጅ ፊልሙን ከ10 ጊዜ በላይ አይቶታል።
ባንኩን ከዘረፈ በኋላ ስሙን ወደ ቶማስ ራንድል ቀይሮ፣ በዋሽንግተን ዲሲ እና በሎስ አንጀለስ እየተዘዋወረ ኖሯል።
ከዚያም ባንኩን ከዘረፈበት በ1000 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኘው ቦስተን መኖር ጀምሯል።
ያለፉትን 40 ዓመታት ያሳለፈው ጎልፍ በማስተማር እና በመኪና መሸጫ መደብር በመሥራት ነበር። ፖሊሶችም ለ25 ዓመታት ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም።
በሳምባ ካንሰር ከሞተ በኋላ ጋዜጣ ላይ የሐዘን መግለጫ ሲወጣ፤ ለ25 ዓመታት በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው ባንክ ዘራፊ መሆኑ ታወቀ።
ከሐዘን መግለጫው ጋር ተያይዞ ከወራት በፊት የተለጠፈው ፎቶ፤ ፖሊሶች በ1960ዎቹ ይፈልጉት የነበረው ግለሰብ ፎቶ መሆኑ ተደርሶበታል።
ባንክ ዘራፊውን ለዓመታት ሲያሳድዱ የነበሩት ጆን ኤልየት ሳይሳካላቸው ሲቀር፤ አሰሳውን ለፖሊስ ልጃቸው ማርሻል ፒተር ኤልየት አውርሰዋል።
ልጅየውም የፖሊስ አባቱን ፈለግ ተከትሎ ሌባውን ሲፈልግ ቆይቷል። የሌባው ማንነት የታወቀው ከሞተ በኋላ ቢሆንም የአባቱን ሕልም እውን እንዳደረገ ይናገራል።
"አባቴ ይህንን ግለሰብ መፈለግ አላቆመም ነበር። በ2020 እስከሚሞት ድረስ ሕልሙ ሌባውን መያዝ ነበር። አሁን ባንክ ዘራፊው ስለታወቀ የአባቴ ነፍስ በሰላም ታርፋለች" ብሏል።












