በኢትዮጵያዊቷ መስከረም የተጠነሰሰው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ቻምፒዮንስ ሊግ ተጀመረ

የመጀመሪያው ቶታልኤነርጂስ ካፍ የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ባለፈው አርብ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ተጀመረ።
ይህ በአፍሪካ ታሪክ የመጀሪያው የሆነው ውድድር ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ ነው።
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ካፍ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ ውድድሩን በማስመልከት ሰፊ ዘገባ እያወጣ ይገኛል።
የካፋ የሴቶች እግር ኳስ ክፍል ነባር ማኔጀር የሆኑት መስከረም ታደሰ ይህንን ውድድር ከጠነሰሱና ካሳኩ ሰዎች መካከል በመሆን ታሪክ መሥራታቸው እየተነገረላቸው ይገኛል።
መስከረም ባለፈው ወር ከካፍ ድረ ገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ይህ ውድድር እውን ሆኖ ማየቴ ትልቅ ደስታ ሰጥቶኛል" ብለው ነበር።
የቶታልኤነርጂስ ካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን 32 የአፍሪካ ክለቦች ቀጣናዊ የማጣሪያ ውድድር አድርገው ነበር።
ይህንን ቀጣናዊ ውድድር ያሸነፉ ስምንት የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች በዚህ ታሪካዊ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።
የማሊ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሞሮኮና የአስተናጋጇ ግብፅ ክለቦች በዚህ የ15 ቀናት ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።
ያለፈው ዓመት የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ አሸናፊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ኬንያ አቅንታ የማጣሪያ ውድድር ማድረጓ አይዘነጋም።
ታድያ በዚህ ታሪካዊ ውድድር ኢትዮጵያን ለመወከል ከጫፍ ደርሳ የነበረችው የንግድ ባንክ ቡድን በማጣሪያው የፍፃሜ ጨዋታ በኬንያዋ ኢሂጋ ኩዊንስ ተሸንፋ መውደቋ ይታወቃል።
ምንም እንኳን ንግድ ባንክ በዚህ ውድድር ላይ አገሯን መወከል ባትችልም ዋና ዳኛ ሊድያ ታፈሰ ወደ ግብፅ በማቅናት ኢትዮጵያን ትወክላለች።
ዋና ዳኛ ሊድያ በውድድር ሁለተኛ ቀን [ቅዳሜ] በሞሮኮዋ አርሚ ሮያል ራባትና በናይጄሪያዋ ሪቨርስ አንግልስ መካከል የሚደረገውን ፍልሚያ ትዳኛለች።
ሊድያን ጨምሮ በፈረንጆቹ 2023 አውስትራሊያ የሚደረገውን የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለመዳኘት የተመለመሉ የአፍሪካ ሴት የእግር ኳስ ዳኞች ይህን ውድድር ይዳኛሉ።
በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ አል-ሰላም ስታድዬም የሚደረገው ይህ ታሪካዊ ውድድር ለአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች ትልቅ መድረክ ሆኖ ታይቷል።
ውድድሩ በሱፐር ስፖርት፣ በቤይን ስፖርት፣ በካናል ፕላስ፣ በካፍ ድረ-ገፅና በፊፋ የዩትዩብ ገፅ እንደሚተላለፍ ካፍ አስታውቋል።













