ኢራቅ የአይ ኤስ የፋይናንስ ኃላፊን መያዟን ገለጸች

የአይኤስ ፋይናንስ ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Iraq Security Media Cell

ኢራቅ ከድንበሯ ውጭ ባደረገችው ዘመቻ የጂሃዲስቱን እስላማዊ መንግሥት የፋይናንስ ኃላፊ መያዟን ገለጸች።

ሳሚ ጃሲም አል-ጃቡሪ በኢራቅ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት "ከሃገር ውጭ ውስብስብ በሆነ መንገድ" በቁጥጥር ስር ውሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ካዲሚ ቦታውን ሳይገልጹ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

አክለውም ጃሲም ወይም ሐጂ ሐሚድ በመባል የሚታወቀው ግለሰብ በሟቹ አቡበከር አል-ባግዳዲ ሥር የአይኤስ ምክትል መሪ ሆኖ ያገለግል ነበር።

አሜሪካ ግለሰቡ እንዲያዝ መረጃ ለሚሰጥ ሰው 5 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር።

የኤፍቢአይ የሪዋርድስ ፎረ ጀስቲስ ድረ ገጽ በበኩሉ "ለአይኤስ የሽብር ተግባራት ፋይናንስን በማስተዳደር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል" ብሏል።

ቡድኑ እአአ በ2014 ሰፊ ግዛትን በኢራቅና በሶሪያ በተቆጣጠረበት ወቅት "በሕገወጥ መንገድ ከነዳጅ፣ ከጋዝ፣ ከጥንታዊ ቅርሶች እና ከማዕድናት ሽያጭ የቡድኑን የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን" ሲመራ ነበር ሲል ገልጿል።

የኢራቃውያን ባለሥልጣናት የሳሚ ጃሲምን መያዝ አይኤስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበታል ይላሉ።

የኢራቅ የደህንነት ሚዲያ ሴል እንዳለው ግለሰቡ እአአ በ 2019 ሶሪያ ውስጥ በተደበቀበት የአሜሪካ ወታደር የወሰደውን ጥቃት ተከትሎ ራሱን ያጠፋው ባግዳዲን ከተካው ከአዲሱ የአይኤስ መሪ አሚር መሐመድ ሰይድ አብዱል ራህማን አል ማውላ ቅርብ ሰው ነበር።

ምንም እንኳን ጃሲም የት እንደተያዘ ካዲሚ ባይገልጹም አንድ ከፍተኛ የኢራቅ ወታደራዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ቱርክ መሆኑን ተናግረዋል። ስለጉዳዩ ከቱርክ ባለሥልጣናት የተሰጠ ምላሽ የለም።

በፈረንጆቹ 2021 መጀመሪያ የኢራቅ መንግሥት ሌላውን ምክትል የአይኤስ መሪ ጃቢር ሳልማን ሳሌህ አል-ኢሳዊን መግደሉን አስታውቋል። የደቡባዊ ኢራቅ የአይኤስ መሪ ጃባር አሊ ፈያድን መግደሉን በተመሳሳይ ገልጿል።

አይኤስ በአንድ ወቅት 88,000 ካሬ ኪ.ሜ ስፋት ያለው እና ከምሥራቅ ኢራቅ እስከ ምዕራብ ሶሪያ የሚደርሰውን ግዛት ተቆጣጥሮ አገዛዙን ወደ ስምንት ሚሊዮን በሚጠጉ ሰዎች ላይ ጥሎ ነበር።

ቡድኑ እአአ በ 2017 በኢራቅ በእንዲሁም እአአ በ2018 በሶሪያ ሽንፈት ቢከናነብም በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች በሁለቱም ሃገሮች ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ይገመታል።