በእርግጥ የአሰላው የአህያ ቄራ ሥራ ጀምሯል?

ሳር የሚግጡ አህዮች

በአሰላ ከተማ ከሰባት ዓመት በፊት ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው እና ከማኅበረሰቡ በተነሳ ተቃውሞ ሳቢያ ሥራውን ለማቆም የተገደደው የአህያ ቄራ መከፈቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

የአሰላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ግለሰብ "ፋብሪካው ድብቅ በሆነ ሁኔታ የአህያ እርድ እያከናወነ ስለመሆኑ በፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ጓደኛዬ አረጋግጦልኛል" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአህዮች ደኅንነት ላይ የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት፣ ዶንኪ ሳንክችዋሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጂአ ሂንደቡ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው ተመልሶ ሥራ መጀመሩን በተመለከተ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃ እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል።

ይህንኑ በተመለከተም ጉዳዩ ለሚመለከተው የግብርና ሚኒስቴር አቅርበው "ፋብሪካው አልተከፈተም" የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

የዶንኪ ሳንክችዋሪ ድርጅት ፋብሪካውን በቀጥታ የመቆጣጠር እና የመጠየቅ ኃላፊነት እንደሌላቸው አመልከተው፣ በአካባቢው በሚገኙ ጋዜጠኞች እና በነዋሪዎች ጉዳዩን ለማጣራት እየጣሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የአሰላ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ቀመሪያ ሳኖ፣ "በአሰላ የሚገኘው የአህያ ቄራ ሥራ ስለመጀመሩ እስካሁን የደረሰን መረጃ የለም" ብለዋል።

ፋብሪካው ከሰባት ዓመት በፊት መዘጋቱን የሚገልጹት ኃላፊዋ "እኛም ብንሆን እስካሁን እንደተዘጋ ነው የምናውቀው፤ ለፋብሪካው ፈቃድ የተሰጠው በፌደራል መንግሥት ነው፤ አሁንም ቢሆን ፈቃዱ ይቀጥል ወይስ አይቀጥልም የሚለውን የሚወስኑት እነርሱ ናቸው" በማለት ባላቸው መረጃ መሰረት "ፋብሪካው ወደ ሥራ እንዳልተመለሰ ነው የምናውቀው" ሲሉ ተናግረዋል።

በአንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች በኩል ፋብሪካው በድብቅ የአህያ እርድ እያከናወነ ነው የሚለውን በአካል በመገኘት እንደሚያጣሩ አክለው ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አህዮች በአገሪቱ እንደሚገኙ ከሚገልጸው ከዶንኪ ሳንክችዋሪ በተገኘ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ባሏት የአህዮች ብዛት በዓለም በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ዶ/ር ቦጂአ ሂንደቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአህዮች ብዛት ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ይሆናል።

አክለውም በአህያ ቁጥር ብዛት ቀዳሚ ከሆኑ አገራት መካከል ቻይና አንደኛ ብትሆንም በአገሪቷ የአህያ እርድ ስለጨመረ የአህዮቿ ቁጥር 11 ሚሊዮን ከነበረበት ወደ ሦስት ሚሊዮን መውረዱን ጥናቶችን በመጥቀስ እናገራሉ።

ዶ/ር ቦጂአ፣ ኢትዮጵያም በአህዮች ቁጥር ብዛት በዓለም በመጀመሪያዎቹ ተርታ መገኘቷ በአህያ እርድ ላይ የተሰማሩ ኢንቬስተሮች ትኩረትን መሳቡን ጨምረው አስረድተዋል።

ከዓመታት በፊት በአሰላ እና በቢሾፍቱ ከተማ የአህያ ቄራ ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱን ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ጋር የሚጻረር ነው በማለት በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞ በማቅረባቸው ቄራዎቹ ሥራቸውን ማቆማቸው ይታወሳል።

የአህያ እርድ ምን ተጽዕኖ አለው?

የዶንኪ ሳንክችዋሪ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቦጂአ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኑሯቸውን በግብርና ላይ ለመሰረቱ አገራት፣ በግብርና ሂደት ውስጥ የአህዮች ሚና የማይተካ መሆኑን ይናገራሉ።

አክለውም በእነዚህ አገራት የአህያ ቄራ መክፈት ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ጫና ያሳድራል ብለዋል።

"እንዲህ ዓይነት ፋብሪካ ለጊዜው ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሚያገለግል ይመስላል፤ ይኹን እንጂ የገጠሩ ሕዝባችን በአብዛኛው ህይወቱ በአህዮች እና ሸሆናቸው ድፍን በሆኑ የጋማ ከብቶች ላይ የተመሰረተ ነው፤ በአብዛኛዎቹ ሸክም የሚጫነው በአህያ ነው፤ አህዮች እየታረዱ ከሄዱ ሸክሙ በቀጥታ ወደ እናቶች እና ሌሎች ሰዎች ይተላለፋል" በማለት ተጽዕኖውን ያስረዳሉ።

በአህያ እርድ ላይ የሚሰማሩ ፋብሪካዎች ወደ አገሪቱ ሲመጡ 'ራሳችን የምናረባቸውን አህዮች ነው የምናርደው' የሚሉ ቢሆንም በተጨባጭ ግን ይህንን ሥራ ላይ ሲያውሉ አይተን አናውቅም ሲሉም ገልፀዋል።

"ራሳቸው የሚያረቡትን አህያ የሚያርዱ ቢሆን መልካም በሆነ ነበር፤ በሌሎች አገሮችም ያለውን ተሞክሮ ብንመለከት በቅድሚያ እንዲህ ያለ ሃሳብ ያቀርባሉ። በተጨባጭ ግን ሥራ ላይ አውለውት አያውቁም። የማኅበረሰቡን አህዮች ነው በደላላ እየገዙ የሚያርዱት።"

"የአህያ እርድ ከማኅበረሰባችን ባህል እና ልማድ ጋር የማይሄድ ነው" ያሉት ዶ/ር ቦጂአ፣ ከዚያም በላይ አህዮች ከገበሬው እጅ ወጥተው ወደ እርድ በሚወሰዱበት ጊዜ በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰው ጫና ቀላል ስለማይሆን ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።