በኬንያ በአህያ እርድ እና ስጋ ንግድ ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነሳ

በቀን አንድ ሺህ የሚሆኑ አህዮች እንደሚታረዱ ይገመታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ መንግሥት የአህያ እርድና ሥጋ ንግድ ላይ ጥሎ የነበረውን እግድ፣ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።

የኬንያ የግብርና ሚኒስትር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በአገሪቱ የአህዮች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄዳቸው የአህያ እርድን አግዶ ነበር።

ኬንያ የአህያ ስጋን እና ቆዳ ንግድን ሕጋዊ ያደረገችው በቻይና ያለውን ፍላጎት ካየች በኋላ በ2012 (እኤአ) ነው።

የግብርና ሚኒስትር የመንግሥትን ውሳኔ የአህዮች ቁጥር እንዲቀንስ ያደረጋል በሚል ተቃውሞ ነበር።

ነገር ግን አንድ የአህያ ሥጋ አቅራቢዎች ድርጅት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ለኪሳራ መዳረጉን እና ሥራ መፍታቱን በመጥቀስ እግዱ እንዲነሳ አቤቱታውን አሰምቷል።

ሐሙስ እለት ጉዳዩን ያየው ችሎት ዳኛ የሆኑት ሪቻርድ ምዎንጎ፣ መንግሥት በአጥጋቢ ሁኔታ ጉዳዩን አላስረዳም በሚል እግዱን ውድቅ አድርገዋል።

በዚህ ውሳኔ መሰረትም በኬንያ በአሕያ እርድ እና ስጋ ንግድ ላይ ፈቃድ ወስደው የተሰማሩ አራት የቄራ ድርጅቶች ስራቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል።

የግብርና ሚኒስቴር የአህያ እርድን ባገደበት ወቅት የቄራ ድርጅቶቹ ወደ በግና ፍየል እርድ ዘርፋቸውን እንዲቀይሩ ተናግሮ ነበር።

ኬንያ ከ10 ዓመት በፊት 1.8 ሚሊዮን አህዮች የነበራት ሲሆን አሁን ግን ወደ 1.2 ሚሊዮን ቁጥራቸው ዝቅ ማለቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ስለ አህዮች ደህንነት የሚሟገተው ብሩክ ኢስት አፍሪካ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የቄራ ድርጅቶቹ በቀን 1000 አህያዎችን ያርዳሉ።

በኬንያ እኤአ ከ2012 ወዲህ የአንድ አህያ ዋጋ በአራት እጥፍ ጭማሪ ሲያሳይ በሕገወጥ መልኩ የአህያ ቆዳ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ደግሞ በቡድን በመሆን ወደ አህያ ስርቆት ላይ መግባታቸው ይነገራል።

በአፍሪካ የአህያ እርድ እና ስጋ ንግድን ካገዱ አገራት መካከል ኡጋንዳ፣ታንዛንያ፣ ቦትስዋና፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ሴኔጋል ይገኙበታል።

በገጠር የሚኖሩ የማህበረሰብ አባላት ውሃ ለመቅዳት አህያን በሰፊው ይጠቀማሉ።

በቻይና ከፍተኛ የሆነ የአህያ ቆዳ ፍላጎት ያለ ሲሆን ባህላዊ መድሃኒት ለማምረት ይውላል።