ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ስለትግራይ እንዳልናገር "ድምጼ ታፍኗል" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርስትያን ፓትርያርክ የሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ግጭት "የአረመኔነት ሥራ" በማለት ጠርተው ብዙ ጊዜ በጉዳዮ ላይ የሰጡት አስተያየት ፈቃድ ባለመሰጠቱ ምክንያት መታገዱን ተናገሩ።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ባለፈው ወር ነው የተቀረፀው ባለው በዚህ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቪዲዮ ላይ በትግራይ ክልል ስላለው ግጭት እና ስለሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት በትግራይ ሚዲያ ሀውስ ላይ በተለቀቀው በዚህ ቪዲዮ ላይ አቡነ ማቲያስ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ጦርነትን "የአረመኔነት ተግባር" ሲሉ የጠሩት ሲሆን እንዲቆም ብዙ ጊዜ መመኮራቸውን ነገር ግን አለመሳካቱን ገልፀዋል።
የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ሕወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወደ ግጭት ከገባ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መሰደዳቸው እና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሲገልፁ ቆይተዋል።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የትግራይን ግጭት በሚመለከት እስካሁን ድረስ ይፋዊ መግለጫ ሳትሰጥ ቆይታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቪዲዮ ላይ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።
የፓትሪያርኩ ጽህፈት ቤትም በአቡነ ማቲያስ የቪዲዮ መልዕክትም ሆነ በትግራይ ግጭት ላይ እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ከሚገኘው አጠቃላይ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነው።
ስድስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ከዚህ ቀደም የደርግ መንግሥትን ተቃውመው በመናገራቸው የተነሳ በስደት ከሰላሳ ዓመት በላይ በውጪ አገር ለመኖር ተገድደዋል።
ቪዲዮውን ማን ቀረፀው?
ከዚህ ቀደም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስም ሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በይፋ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው ግጭት ሲናገሩ አልተሰማም።
እንደ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ይህ የአቡነ ማቲያስ ቪዲዮ የተቀረፀው ከቤተክርስትያኒቱ ጋር በቅርበት የሚሠራው እና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የ'ብሪጅስ ኦፍ ሆፕ' ባልደረባ፣ ዴኒስ ዌድሊ ነው።
ቪዲዮው በአዲስ አበባ በፓትርያሪኩ ጽህፈት ቤት መቀረፁን የተናገረው ዴኒስ ፓትሪያሪኩን በጽህፈት ቤታቸው በጎበኘበት ወቅት ስልኩን በማውታት ". . . መናገር የሚፈልጉ ከሆነ አሁን መቅረጽ እንችላለን" እንዳላቸው ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ገልጿል።
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ የቤተክርስትያኒቱ ተወካዮች አቡነ ማቲያስ መልዕክታቸው ለሕዝብ እንዲደርስ እንደፈቀዱ አረጋግጠዋል።
"ድምፄ ታፍኗል"
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በተደጋጋሚ በትግራይ ክልል ስላለው ግጭት የሰጡት አስተያየት ፈቃድ ባለመሰጠቱ ምክንያት መመለሱን በዚህ ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል።
መልዕክታቸው ለሕዝብ እንዳይደርስ "እየታፈነ" እንደሚቀር ተናግረው እነማን ፈቃድ እንደሚሰጡ እና እንደሚከለክሉ የተናገሩት ነገር የለም።
"እኔ የምናገረው ዓለም የሚያውቀውን ነው" ያሉት ፓትሪያርኩ፣ እስካሁን ድረስ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስ "በፍርሃት አፋቸው ተለጉሞ፣ በተጽዕኖ አለመናገራቸውን" ገልፀዋል።
በትግራይ ሚዲያ ሐውስ በትናንትናው ዕለት በተለቀቀው በዚህ ቪዲዮ ላይ ሚያዚያ 7/2013 ዓ.ም ለቤተክርስትያኑ ቴሌቪዥን ቃለምልልስ መስጠታቸውን አስታውሰው መታገዱን ጨምረው ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ሚዲያ የሚነገረውን እኛ እንዳንናገር ተከልክለናል ያሉት አቡነ ማቲያስ፣ በትግራይ የሚደርሰው "የንፁኀን ዜጎች ግድያ እና ስቃይ" ሁሌም አእምሯቸውን እንደሚያውከው በመግለጽ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
"በትግራይ ያለው ግጭት ከሁሉም ይብሳል"
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዚህ የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ በትግራይ ክልል የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ችግር መኖሩን የተናገሩት አቡነ ማቲያስ ነገር ግን "የትግራይን ያክል አይደለም" ሲሉ የጉዳዩን ግዝፈት ተናግረዋል።
የትግራይ ችግር "እጅግ የከፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት" ነው በማለት እርሳቸውም ሆኑ አለም ይህንን እንደሚያውቅ አብራርተዋል።
አቡነ ማቲያስ በዚሁ መልዕክታቸው ላይ በማህበረ ዴጎ የተፈፀመውን ግድያ በማንሳት ንፁኀን ዜጎች ተገድለው ገደል መጣላቸውን በሥርዓት አለመቀበራቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' ፕሮግራም ባደረገው ምርመራ በማህበረ ዴጎ ከተማ አቅራብያ 15 ወንዶች የተገደሉበት አንድ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ማግኘቱን ገልፆ ነበር።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ግን ውንጀላውን አስተባብሎ ነበር።
አቡነ ማቲያስ አክለውም በትግራይ ሴቶች እንደሚደፈሩና እንደሚሰቃዩ ገልፀው፣ "በሴቶች ላይ የደረሰው ዘላለም በአእምሯቸው የሚቀር ጠባሳ ነው እያስቀመጡባቸው ያሉት" ብለዋል።
ድርጊቱንም "ቆሻሻ" በማለት የኮነኑት ፓትርያርኩ እጅግ በጣም ማዘናቸውንም አክለው ተናግረዋል።
በትግራይ የተቀሰቀሰው ግጭት ስድስት ወር መያዙን ያስረዱት ፓትሪያርኩ መፍትሔ አለማግኘቱን ጨምረው አስረድተዋል።
"ይህን ግፍ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚመልሰው የራሱ ዳኝነት ይኖረዋል" በማለት ሕዝብ ክፉኛ እያለቀ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሟጋች ቡድን፣ አምንስቲ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ለስድስት ወራት በዘለቀው የትግራይ ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተካሂደዋል ብሏል።
ከዚህ ቀደም አምንሲቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአክሱም በሰብዓዊ ዜጎች ላይ በኤርትራ ወታደሮች ስለደረሰው ጭፍጨፋ ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።
አምንስቲ በትግራይ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ መቶ ሺዎች ክልል ውስጥ ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም 63 ሺህ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰድደዋል ብሏል።
አምነስቲ በተለያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በጋራ መድፈርን ጨምሮ ታዳጊና አዋቂ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈፀሙ ማስረጃዎች አሉ ይላል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በትግራዩ ግጭት ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተመርምረው ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ለሕግ ይቀርባሉ ብለው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአፍሪካ ሕብረት ሰብዓዊ አጥኒ ኮሚሽን ጋር የተፈጸሙ የመብት ጥሰተኞችን በጋራ እንደሚመረምሩ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ከመብት ጥሰቶቹ ጋር ተያይዞ ሰሙ በተደጋጋሚ ለሚነሳው የኤርትራ ጦር በተመለከተ አገሪቱ መንግሥት ከሶቹ መሠረተ ቢስ ናቸው ሲል አጣጥሎ ነበር።
ንብረት ዘረፋ
"የትግራይ ሕዝብ ንብረቱ ተዘርፏል፣ መብቱ ተገፏል ሕይወቱን ተነጥቋል" ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ "ካላጠፋንህ ብለው እስካሁን ድረስ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ" ብለዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ ወቅት ትግራይ ውስጥ "የዘር ማፅዳት ወንጀል" ተፈጽሟል ያሉ ሲሆን ድርጊቱን ከማውገዝ በተጨማሪ "ሙሉ ተጠያቂነት" እንዲኖር ጥሪ አቅርበው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በትግራይ ክልል 'የዘር ማጽዳት' ድርጊት ተፈጽሟል የሚለው ክስ በፍጹም "ተጨባጭ ያልሆነና ሐሰተኛ" ነው ሲል በወቅቱ አስተባብሏል።
ለዚሁ ክስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ምላሽ ሲሰጥ "በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘረ ተጨባጭነት የሌለውና ሐሰተኛ ክስ ነው" ብሎታል።
መግለጫው ጨምሮም መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ ያካሄደው ዋነኛው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅትና ከተጠናቀቀ በኋላ ሆን ተብሎ በክልሉ ውስጥ ማንንም ኢላማ ያደረገ "ዘር ማጽዳት" ተብሎ የሚጠቀስ ድርጊት አልተጸመም በማለት ክሱን የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል።
አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ክልል ተከሰተ ስላሏቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች ተአማኒ መረጃዎች እንዳሉ አመልክተው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
አቡነ ማቲያስ በቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ ገበሬዎች እርሻቸውን እንዳያርሱ ተከልክለዋል ያሉት ፓትርያርኩ፣ "በአብያተ ክርስትያናት ላይ ይተኩሳሉ፣ በገዳማት ላይ ይተኩሳሉ" በማለት በተለየዩ አብያተ ክርስትያናት ደርሷል ያሉትን ጥቃት ዘርዝረዋል።
በደብረ ዳሞ በተተኮሰ መድፍ የመነኮሳቱ ቤት መፍረሱን፣ አንድ የእምነቱ አባት መገደላቸውንም ተናግረዋል።
በዋልድባ ገዳም የሚገኙ መነኮሳት ከሚኖሩበት ገዳም እንዲወጡ መደረጋቸውን፣ አዛውንቶች ጎዳና መውደቃቸውን፣ በአሲምባ ባህታዊ ዘወንጌል መመታቱን፣ በማርያም ደናግላት ደግሞ ክብረ ዓል ላይ የነበሩ ንፁኀን መገደላቸውን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ ይውሰድ
ዓለም አቀፍ መንግሥታት የንፁኀን ግድያ የሚቆምበትን መንገድ እንዲፈልጉ ሲሉ ተማጽኖአቸውን አቅርበዋል።
አቡነ ማትያስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም ቤተክያርስትያናት ይህንን ጉዳይ አይተው የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርባል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ጉዳዮች ተቋማት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች በአፋጣኝ ዕርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በክልሉ ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ዜጎች የሚቀርበውን ሰብዓዊ እርዳታ ከ70 በመቶ በላይ እያቀረበ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።
















