ትግራይ ፡ በኢትዮጵያ የትግራይ ግጭት የኤርትራ ሚና ምን ነበር?

ፕሬዝደንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተለዋዋጩ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ አንድ ሰሞን ከኢትዮጵያ ጋር ሰላማዊ ያልሆነ ግንኙነት የነበራቸው የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አጋር ሆነዋል። ከህወሓት ጋር በነበረው ግጭት ለፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

በቅርቡ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኤርትራ፤ ከህወሓት ጥቃት በማፈግፈግ ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮችን አብልታለች፣ አልብሳለች እንዲሁም አስታጥቃለች ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እርዳታ የኢትዮጵያ ወታደር ተመልሶ 250 ሺህ ወታደሮች ያለውን ሕወሓት እንዲወጋ አስችሎታል ብለው ነበር።

አሁን በፌዴራል መንግሥቱ ከሥልጣን የተወገደው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ትግል ላይ ሳለ በሽምቅ ውጊያ ይታወቅ ነበር።

"የኤርትራ ሕዝብ ከእኛ ጎን የቆሙ ወገኖቻችን እንደሆኑ በአስቸጋሪ ወቅት አሳይተውናል" ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕሬዝደንት ኢሳያሳ የኤርትራ ወታደሮች ለአስርታት በኢትዮጵያ መንግሥት የሥልጣን መንበር ላይ የቆውን ህወሓትን እንዲዋጉ ልከዋል የሚለውን ባያምኑም ኤርትራ ላደረገችው ድጋፍ የሰጡት እውቅና ግን ትልቅ ነበር።

የኤርትራ ሆስፒታል ተደብድቧል ስለመባሉ

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን አብረው እየተዋጉ ነው የሚለው ክስ መጀመሪያ የተሰማው ከህወሓት በኩል ነበር። አልፎም ግጭቱን ሸሽተው የተሰደዱ ነዋሪዎችና አገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ይህንን ደግመውት ነበር።

"ኢሳያስ ወጣት ኤርትራዊያንን ወደ ትግራይ ልኮ ለሞት እየማገደ ነው። ጦርነቱ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት የበለጠ ይጎዳል። ነገር ግን ኢሳያስ ሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ መቆየቱ አይቀሬ ነው። ሰዎች ለነፃነታቸው ሳይሆን ለመኖር እንዲፋለሙ እያደረገ ነው" ይላል አገሩን ጥሎ የተሰደደው ኤርትራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጳውሎስ ተስፋጊዮርጊስ።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኤርትራ በትግራይ ክልል በሚደረግ ውጊያ ስለመሳተፏ የሚያስረግጥ "አስተማማኝ መረጃ" አለ ብሎ "ስጋቱን" ገልፆ ነበር።

ነገር ግን ሁለቱም መንግሥታት ይህንን ያስተባብላሉ።

የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ "ይህ ፕሮፖጋንዳ" ነው ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በፈረንጆቹ 2018 ኢትዮጵያ የገባችውን ታሪካዊ ስምምነት ተከትሎ ለኤርትራ ከሰጠችው መሬት ላይ ውጭ ምንም ዓይነት ኤርትራዊያን ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የሉም ሲሉ አረጋግጠውልኛል ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የደረሱት ስምምነት ለ20 ዓመታት "ጦርነትም-ሰላምም የራቀው" የተባለው ግንኙነት ማብቂያ ሆኗል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ቢያንስ 100 ሺህ ያክል ሰዎች ሞተዋል።

ይህ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የትግራይ ክልል የቀድሞ አስተዳዳሪ ህወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ጦርነቱ እስከሚጀመርበት ጊዜ ድረስ ግን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስከተለውን መሬት ለኤርትራ አሳልፋ አልሰጠችም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር መገናኛ ብዙሃን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ወደ ትግራይ ክልል መግባት እንዳይችሉ ከባድ አድርጎታል። ይህም ገለልተኛ አካላት በሁሉም ወገን ተፈፀሙ የተባሉ ጥፋቶችን ገብተው እንዳያጣሩ አድርጓል።

ተፈፅመዋል ከተባሉ ጥፋቶች መካከል ከኤርትራ በኩል በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ድብደባ የአንድ ሆስፒታል መመታት አንዱ ነው።

ኤርትራ ተደብድቧል ስለተባለው ሆስፒታል ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ተቋም ግን በዚህ አይስማማም። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በትግራይ ክልል አንድም ሰላማዊ ዜጋ አልሞተም ብሏል።

"ይህ ጦርነት የተካሄደው እጅግ በጣም ድቅድቅ በሆነ ጨለማ ውስጥ ነው። ጦርነቱ ስላስከተለው ጉዳት ማንም ምንም አያውቅም" ይላሉ ነዋሪነታቸው ኬንያ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ ራሺድ አብዲ።

በግጭቱ ከተጎዱ ስፍራዎች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በግጭቱ ከተጎዱ ስፍራዎች አንዱ

ኤርትራዊያን ወታደሮች ንብረት ዘርፈዋል ስለመባሉ

ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነው ተንታኝ አሌክስ ደ ዋል የተባበሩት መንግሥታት ምንጮች ነገሩኝ እንደሚለው ከሆነ አምስት ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባትና ከኢትዮጵያ ክልሎች ደሃ የሆነችው "ትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎች ተፈናቅዋል።"

"ይህ የሚቀጥል ከሆነ በክልሉ የጅምላ ረሃብ ሊከሰት ይችላል። ሕዝቡ ግፍ ስለተፈፀመበት ቁጣ ሊቀስቀስ ይችላል" ይላል ደ ዋል።

ደ ዋል፤ የሐይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታማኝ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደሚለው የኤርትራ ወታደሮች ቤት ንብረት በመዝረፍ ተሳትፈዋል።

"እንደምንሰማው ከሆነ በርና የመታጠቢያ ቤት ዕቃዎችን ሳይቀር ዘርፈዋል" ይላል ደ ዋል።

ሌሎች ኤርትራዊያን እንደሚሉት ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ኤርትራዊያን ወደታሮች ከህወሓት ኃይሎች ጋር በርካታ አምባዎች ላይ ጦርነት ገጥመዋል። አክለው አንዳንዶቹ ኤርትራዊያን ወታደሮች የኢትዮጵያ ወታደር መለዮ ለብሰው ነው ሲዋጉ የነበረው ይላሉ።

ኤርትራ፤ ትግራይ ክልል ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደሮች የሉኝም ትላለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም "እኛ አልተሳተፍንም" ይላሉ።

አሁን ከአገር ውጭ በስደት የሚኖሩት የቀድሞው የኤርትራ ዲፕሎማት አብደላ አደም እንደሚሉት እሳቸው በአካላ የሚያውቋቸው ወታደሮች ሳይቀሩ በነበረው ግጭት ቆስለዋል።

በደቡብ ኤርትራ የምትገኘው ሰንአፈ ውስጥ ካለ ሆስፒታል ቢቢሲ መስማት እንደቻለው ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ቆስለው ሲታከሙ ነበር።

'ኢሳያስ ወሓት እንዲከስም ይፈልጋሉ'

ከኤርትራ የተገኙ ምንጮች አንደሚሉት ከሆነ በማዕከላዊ ኤርትራ ሃጋዝ ከተማ የኢትዮጵያን ወታደሮች ተሰባስበው ነበር፤ የቆሰሉ ወታደሮች ደግሞ በአቅራቢያው በሚገኘው ጊላስ ወታደራዊ ሆስፒታል ሲታከሙ ነበር።

ዩናይትድ ኪንግደም የሚኖረው ኤርትራዊው ምሁር ጋይም ክብረዓብ ኢሳያስ ወታደሮቻቸውን ወደ ትግራይ የላኩት "ህወሓት እንዲጠፋ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው" ይላል።

ይህ ከ1990 የኢትየ-ኤርትራ ጦርነት ጀምሮ አንስቶ የኤርትራው መሪ ዋነኛ አላማ ሆኖ ቆይቷል ይላል ጋይም።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት በገጠሙ ጊዜ ህወሓት የትግራይ ክልልን ከማስተዳደር ባለፈው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራው ግንባር የበላይ ነበር።

"ከ1990-92 (እአአ) በነበረው ጦርነት ህወሓት ባድመን በመውሰድ የኤርትራውን መሪ አሳፍሯል። ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መሬቱን ለኤርትራ ቢወስንም ህወሓት ግን ለ18 ዓመታት ወታደሮቹን ከሥፍራው ለማስወጣት ፈቃደኛ አልነበረም ነበር።"

"ፕሬዝደንቱ [ኢሳያስ] ይህን ዕድል ለማግኘት ዓመታት ጠብቀዋል። ነገር ግን ህወሓት የፕሬዝደንቱን ትዕግስ ንቆት ነበር" ሲል ይተነትናል ምሁሩ።

ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ሲከፈት የነበረው ደስታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ሲከፈት የነበረው ደስታ

ከሰላም ወደ ግጭት

የኢሳያስ ደጋፊዎች የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል አልገቡም ይላሉ። ነገር ግን ባድመና አካባቢዋን በመያዝ የኤርትራን መሬት መልሰዋል ባይ ናቸው።

በዚህ ሐሳብ ጳውሎስ አይስማማም። "ባድመ በኤርትራ እጅ ገብታ ነበር። ነገር ግን ይህ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም። ምክንያቱም የኢሳያስ ዋና ዓላማ ይህ አልነበረም። የእሱ ዓላማ የነበረው ህወሓትን ማድቀቅ ነው።"

"ዐብይ ሰላም መላሽና ለውጥ አምጪ ሆኖ ነው ሥልጣን የያዘው። ነገር ግን ህወሓትን መበቀል ለሚለው ዓላማ እጁን ሰጠ። ይህ ደግሞ ኢሳያስ የሚፈልገው ነው" ይላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከህወሓት ጋር ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሞክረናል ይላሉ። ነገር ግን ወደ ግጭት ለመግባት የተገደድነው ህወሓት የሰሜን ዕዝን ተቆጣጥሮ መንግሥት ለመገልበጥ በመሞከሩ እንደሆነ ያክላሉ።

ምንም እንኳ ኢሳያስ ለእርዳታ እጃቸውን ቢዘረጉም የኤርትራ መገናኛ ብዙሃን ግን ስለ ግጭቱ አንድም ዘገባ አልሠሩም። ሌላው ቀርቶ ህወሓት ግጭቱ የተጀመረ ሰሞን ወደ አሥመራ ስላወሰነጨፋቸው ሚሳዔሎችና ስለተሰማው ከባድ ፍንዳታ ምንም ነገር አልተባለም።

"የኤርትራ ቲቪ ሶሪያ ውስጥ ስለፈነዱ ቦምቦች ዜና እየሠራ አሥመራ ላይ ሚሳዔል ሲተኮስ ምንም አላለም" ይላሉ የቀድሞ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣን ዳዊት ፍሰሐዬ።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ መስቀል በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት "የህወሓትን የመጨረሻና ተገማች ነገር ግን እርባና ቢስ እርምጃ ማስተጋባት ምንም ጥቅም የለውም" ብለው ነበር።

ታፍነዋል ስተለባሉ ስደተኞች

ኤርትራ ውስጥ የበይነ መረብ አገልግሎት እጅግ የተገደበ ነው። አልፎም ምንም ዓይነት ነፃ ሚድያም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም።

ኤርትራ ውስጥ ከ20 ዓመታት በፊት ለእሥር የተዳረጉት 11 ፖለቲከኞችና 17 ጋዜጠኞች የት እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም።

በብሔራዊ አገልግሎት አማካይነት በወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ግዳጅ የሆነባት ኤርትራ ለዜጎቿ በቂ የሆነ የሥራ ዕድል የላትም። ይህም በርካታ ወጣቶች አገር ጥለው እንዲወጡ አድርጓል።

በትግራይ ክልል ብቻ 100 ሺህ ያህል ኤርትራዊያን ስደተኞች በተባበሩት መንግሥታት መጠለያዎች ውስጥ ይኖራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ወኪል፤ ስደተኞች ስለመገደላቸው እንዲሁም ታፍነው በአንድ ፓርቲ ወደ ምትተዳደረው አገር ስለመወሰዳቸው "ከብዙ ታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ" ይላል።

ድርጅቱ ስደተኞቹን ማን አፍኖ እንደወሰዳቸው ያለው ነገር ባይኖርም፤ አንድ ስደተኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው ኤርትራዊያን ወታደሮች ስደተኞችን በከባድ መኪና እየጫኑ ከአዲግራት ከተማ ወደ አዲ ቋላ ወስደዋቸዋል።

ኤርትራ በዚህም ጉዳይ ምንም ዓይነት አስተያት አልሰጠችም። ነገር ግን ከዚህ ቀድሞ የስደተኞች ኮሚሽኑ የኤርትራን ሕዝብ ለማራቆት "ሰፊ ዘመቻ" ጀምሯል ስትል ከሳ ነበር።

ዳዊት፤ የኤርትራ አገዛዝ በፍፁም ይለወጣል ብሎ አያስብም።

"ኤርትራ ውስጥ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ለውጥ የለም። ምክንያቱም አገዛዙ ይህን አይፈልግም። የህወሓት መጥፋትም ምንም ዓይነት ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም። ለውጥ መጠበቅ የማይፈታ ህልም ነው" ይላል።