ሐይማኖት ፡ ኤርትራ ለዓመታት በእስር የቆዩ የይሖዋ ምስክሮችን ከእስር ለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራ ውስጥ ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩ 28 የይሖዋ ምስክሮች እምነት ተከታዮችን ከእስር እንደለቀቀች ተገለጸ።
በእስር ላይ የቆዩት የእምነቱ ተከታዮች ከእስር የተለቀቁት የእስር ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።
ኤርትራ ከ1987 ዓ.ም ገደማ ጀምሮ የይሖዋ ምስክሮች እምነት ተከታዮችን ዜግነት የሰረዘች ሲሆን ክስ ሳይመሰረትባቸው ለእስርም ሲዳረጉ ቆይተዋል። የመታወቂያ ደብተርም ማግኘት አይችሉም።
የይሖዋ ምስክሮች ለእስር ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በአስገዳጁ የኤርትራ ወታደራዊ ብሔራዊ አገልግሎት የመሳተፍ ፍላጎት ስለሌላቸው ነው።
የይሖዋ ምስክሮች ባወጣው መግለጫ አባላቱ ከአምስት እስከ 26 ዓመታት በእስር ካሳለፉ በኋላ መለቀቃቸውን አስታውቋል።
የይሖዋ ምስክሮች ከተለቀቁት የእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ አሁንም 24 አባላቱ በእስር እንደሚገኙ አስታውቋል።
ኤርትራ ነጻ አገር ሆና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የመሪነት ስልጣኑን ከያዙ ከአንድ ዓመት በኋላ የይሖዋ ምስክሮችን ዜግነት እንደተሰረ ይነገራል።
ኤርትራ በዓለማችን ከሚገኙ የሰዎችን መብት ከሚገድቡ አገራት መካከል አንዷ ነች። በኤርትራ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የላትም። በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ሕገ-መንግሥትም ሥራ ላይ ውሎ አያውቅም።
በኤርትራ ፍቃድ ያላቸው እና መንግሥት እውቅና የሰጣቸው ሐይማኖቶች አራት ብቻ ናቸው። የኦርቶዶክስ ክርስትና፣ የሱኒ እስልምና፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን እና የሉተራን ወንጌላዊ ቤተ-ክርስቲያን ናቸው።
ሌሎች የእምነት ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ እንደ ሕገ-ወጥ ነው የሚቆጠሩት መንግሥት የውጪ አገራት አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ናቸው በማለት ነው።
የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሐይማኖት ነጻነት ኮሚሽን የ2019 ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከሆነ፤ ዛሬ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን በእምነታቸው ምክንያት ለእስር እንደተዳረጉ ናቸው።














